የዲጂታል ልማትና አገልግሎት በኢትዮጵያ መሰረታዊ ለውጥና ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ልማትና አገልግሎት በኢትዮጵያ መሰረታዊ ለውጥና ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል
ሆሳዕና፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ልማትና አገልግሎት በኢትዮጵያ መሰረታዊ ለውጥና ተጨባጭ ውጤት የመጣበት መሆኑን በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ፡፡
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በተለይም በተቋማት አገልግሎት አሰጣጥና በዜጎች የአኗኗር ዘይቤ ላይ የሚታይ ለውጥ የመጣበት በመሆኑ ለቀጣዩ ዕቅድ የላቀ ስኬት መስራት አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።
ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስኬት በመነሳት ተደራሽነትን፣ ለዜጎች እኩል እድል መፍጠርንና በዜጎችና በተቋማት መካከል መተማመንን የማጎልበት ዓላማን በመሰነቅ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ መደረጉ ይታወቃል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ መምህርት ፀጋነሽ ሞገስ፤ በኢትዮጵያ የዲጂታል ልማት በተለይም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሰረታዊ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
የአሰራር ፍጥነትን፣ ቁጥጥርንና ተጠያቂነትን እውን በማድረግ ለዜጎች ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት በሚደረገው ጥረት የዲጂታል አገልግሎት ትልቁን ድርሻ መያዙን አንስተዋል።
የኮደርስ ስልጠና፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ብሔራዊ መታወቂያ የዘርፉን አገልግሎት ይበልጥ እያሳለጡ መሆኑን አንስተው የቴሌብር፣ የባንክና ሌሎችም የተቋማት አገልግሎቶች እመርታዊ ለውጥ አምጥተዋል ብለዋል።
የዲጂታል ልማት በድምሩ በኢትዮጵያ መሰረታዊ ለውጥና ተጨባጭ ውጤት የመጣበት መሆኑን ገልጸው፣ ዜጎች በአንድ ቦታ የተለያዩ አገልግሎቶችን በማግኘት እንግልትን እንዳስቀረ ተናግረዋል።
ከዚህ በመነሳት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የተያዘውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ይገባል ሲሉ መምህርቷ ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ መምህር መሳይ አስቻለው፤ በ2025 የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ መሰረተ ልማትን ከመዘርጋት ጀምሮ በቴክኖሎጂ የተደራጀ ተቋምና የተሻለ ግንዛቤ ያለው ትውልድ በመገንባት ረገድ ተጨባጭ ስኬት ተመዘግቧል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፈንታ ለመወሰን በቴክኖሎጂ ልማት ላይ መስራት ለነገ የማይባል ሥራ መሆኑን አንስተው ለተያዘው እቅድ መሳካት የሁላችንም ጥረትና ትብብር ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተለይ ዲጂታል 2030 እንደሀገር የተጀመረውን ራዕይ የሚያሳካ መሆኑን ገልጸው፣ ዜጎች በተለይ ወጣቱ በቴክኖሎጂ ብቁ እንዲሆን የተጀመሩ ሥራዎች ለዚህ ስኬት ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያን እድገትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እውን ለማድረግ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የልማት ግብ ማሳካት እንደሚገባም አጽእኖት ሰጥተዋል።
በተለይ ቴክኖሎጂ የሀገርን ኢኮኖሚና ማህበረሰቡን ለማነቃቃት ካለው ጠቀሜታ አንጻር ታይቶ ዘርፉን ለማሳደግ የተጀመረው ሥራ መጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።