በክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦትን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስችል ስራ ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦትን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስችል ስራ ተጀምሯል
አሶሳ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የምርጥ ዘር አቅርቦትን በራስ አቅም ለመሸፈን የማምረት ስራ መጀመሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በአቡራሞ ወረዳ በሮዳስ የእርሻ ልማት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በ95 ሄክታር ማሳ እየለማ በሚገኘው የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት ማሳ የመስክ ምልከታ አካሂደዋል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር አብዱሰላም አብዱልጀሊል እንደተናገሩት፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የዘር ጥራት ወሳኝ ነው።
በክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦትን በራስ አቅም ለመሸፈን በተደረገው ጥረት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ከ9 ሺህ 400 በላይ ሄክታር ማሳ በምርጥ ዘር ብዜት በሰብል መሸፈኑን ተናግረዋል።
ሶስት ድርጅቶች በክልሉ የዘር ብዜት ላይ ብቻ እንዲሰማሩ በማድረግ የበቆሎ፣ ማሽላ፣ አኩሪአተር፣ ሩዝ እና ሌሎች ሰብሎችን እያለሙ መሆኑን ጠቁመው በአሁኑ ሰዓት ምርቱ ለመሰብሰብ ዝግጁ ነው ብለዋል።
ክልሉ ለምርጥ ዘር ብዜት የሚሆን ሰብል ማምረት መጀመሩ አርሶአደሩ ምርጥ ዘርን በአቅራቢያው እንዲያገኝ እና አላስፈላጊ ወጪን ለማስቀረት እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።
የሮዳስ እርሻ ልማት ባለቤት ሞላ ተመስገን በበኩላቸው፤ በዘንድሮው ዓመት በአቡራሞ፣ ባምባሲ እና ዳንጉር ወረዳዎች ላይ 135 ሄክታር ቢ ኤች 661 የተሰኘ የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዘሩ ለአካባቢው ስነምህዳር ተስማሚ መሆኑ በባለሙያዎች የተረጋገጠ እንደሆነ ተናግረው የክልሉ ግብርና ቢሮ አስፈላጊውን ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የአካባቢው አርሶአደሮች የድርጅቱን ተሞክሮ በመውሰድ በምርጥ ዘር ብዜት ልማት ላይ እየተሳተፉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።