የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ሉአላዊነት በማረጋገጥ ከተረጂነት የማላቀቅ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ሉአላዊነት በማረጋገጥ ከተረጂነት የማላቀቅ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ድሬዳዋ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ሉአላዊነት በማረጋገጥ ከተረጂነት ለማላቀቅ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክርቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ሻኪር አህመድ ተናገሩ።
በድሬዳዋ አስተዳደር ለገጠር ቀበሌ አመራሮችና የግብርና ባለሙያዎች የበጋ መስኖ እና የተፋሰስ ልማት መርሃ ግብር ማስጀመሪያ ስልጠና ዛሬ ተሰጥቷል።
በስልጠናው ላይ ተገኝተው መመሪያ ያስተላለፉት የአስተዳደሩ ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ሻኪር አህመድ በወቅቱ እንዳሉት፤ የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ከተረጂነት የማውጣቱ ሂደት ስኬታማ እየሆነ ይገኛል።
በአስተዳደሩ ያሉትን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ፀጋዎች በአግባቡ በመጠቀም እና በመንከባከብ የምግብ ሉአላዊነትን የማረጋገጡ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
የእርሻ መሬት፣ የውሃ ሃብትና የሰው ኃይልን በማቀናጀት የግብርና ስራውን ለማላቅ በሚሰራው ሥራ የተፋሰስ ልማት ቁልፍ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።
የአስተዳደሩ ገጠር ቀበሌ አመራሮች፣ እንዲሁም የግብርና ባለሙያዎች የተፋሰስ ልማቱ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስገኝ እና ልማቱ ዘላቂነት እንዲኖረው የተቀናጀ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፋሰስ እና የአነስተኛ መስኖ ልማቶች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ከተረጂነት እንዲላቀቁ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በተለይም በተራቆቱ ተፋሰሶች ላይ የተካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ምንጮችን በማጎልበት፣ ተስማሚ ስነምህዳር በመፍጠርና የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻን በማሳካት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማስቻሉን ነው ያወሱት።
በዚህ ዓመት አስተዳደሩ በሚያከናውናቸው ልማቶችና ድጋፎች ታግዘው 27 ሺህ የሚጠጉ የገጠር ቤተሰቦች የምግብ ሉአላዊነትን ሙሉ በሙሉ ያረጋግጣሉ ብለዋል።
በዛሬ ዕለት የተሰጠውን ስልጠና ወደታች በማውረድ እና ወጥ የሆነ አስተሳሰብ በመፍጠር የተጀመሩትን ልማቶች በላቀ ደረጃ ለማሳደግ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በዘንድሮው የበጋ ተፋሰስ ልማት በ5ሺህ 550 ሄክታር የተራቆቱ መሬቶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባራት ይከናወናሉ ያሉት ደግሞ በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና የገጠር መሬት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አሊይ አህመድ ናቸው።
በስልጠናው ላይ የተካፈሉት የቀላድ ገጠር ክላስተር ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ አህመድ ሁሴን እና የገንደ ሪጌ የገጠር ቀበሌ ግብርና ባለሙያ ወይዘሮ አስቴር ዘለቀ በአፈርና ውሃ ሃብት ጥበቃ ላይ የተጀመረውን የተፋሰስ ልማት በማጠናከር የምግብ ሉአላዊነት የማረጋገጥ ጉዞን እናሳካለን ብለዋል።