ቀጥታ፡

በክልሉ የባሕል ፍርድ ቤቶች ስራ መጀመር የማሕበረሰቡ ነባር እሴት እንዲጠናከር ያግዛሉ

ባሕርዳር፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶች እውቅና አግኝተው ስራ መጀመራቸው የማሕበረሰቡ ነባር እሴት እንዲጠናከር እንደሚያግዙ ተመላከተ።

የክልሉ የባሕል ፍርድ ቤቶች እውቅና አሰጣጥና ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር የክልሉና የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በባሕርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ የባሕል ፍርድ ቤቶች የማሕበረሰቡን ችግር በመፍታት ዘመናትን የተሻገሩ እሴቶች በመሆናቸው እንዲጠናከሩ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት የባሕል ፍርድ ቤቶችን ሚና በመረዳት ሕጋዊ እውቅና ተሰጥቷቸው እንዲሰሩ ማድረጉ ችግሮችን በጥበብና በብልሃት ለማለፍ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

የባሕል ፍርድ ቤቶቹ አቅመ ደካማ የሕብረተሰብ ክፍሎች በቅርበት ፍትሕ እንዲያገኙ በማገዝ ረገድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል።


 

የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ማሕበረሰቡ የሚያጋጥመውን ችግር የሚፈታበት ከጥንት ጀምሮ ይዞት የመጣ የሽምግልና ስርዓት እንዳለው ገልጸዋል።

ይህን አሰራር በባሕል ፍርድ ቤቶች በሕግ አግባብ በማደራጀትና ሕጋዊ እውቅና በመስጠት ወደ ስራ ማስገባት መቻሉ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ይሕም መንግስት ችግሮችን በንግግርና በውይይት በመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የያዘውን ግብ ለማሳካት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በየአካባቢው ሴቶች፣ ሕጻናትና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መብትና ጥቅም በማስከበር በኩልም ሚና ይኖራቸዋል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል መንግስት ወደ ስራ ላስገባቸው የባሕል ፍርድ ቤቶች ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።


 

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር ለባሕል ፍርድ ቤቶች መጎልበት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በክልሎች ለባሕል ፍርድ ቤቶች የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

ባሕልን መሰረተ ያደረገ የግጭት አፈታት አሰራርን ለማጎልበት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ደግሞ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አለምአንተ አግደው ናቸው።


 

የክልሉ መንግስት የባሕል ፍርድ ቤቶችን በሕግ አግባብ በማደራጀትና አሰራር በማበጀት ወደ ስራ የሚገቡበትን ሁኔታ ሲያመቻች መቆየቱን አንስተዋል።

ሽምግልናን ጨምሮ 15 ሌሎች ማህበራዊ እሴቶች በክልሉ የባሕል ፍርድ ቤቶች እውቅና እንዲሰጣቸው መደረጉን ጠቁመው፤ የባሕል ፍርድ ቤቶቹ ተጠሪነታቸው ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ባሕላዊ ፍርድ ቤቶቹ በአካባቢያቸው ባሕልና ወግ መሰረት ሕብረተሰቡን እንዲያገለግሉ የሚያስችል መሆኑን በማብራራት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም