የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ እንዴት ይፈጸም ወደሚል ዓለም አቀፍ ቅቡልነት ያለው የዲፕሎማሲ ስኬት ማሸጋገር ተችሏል - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ እንዴት ይፈጸም ወደሚል ዓለም አቀፍ ቅቡልነት ያለው የዲፕሎማሲ ስኬት ማሸጋገር ተችሏል - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ እንዴት ይፈጸም ወደሚል ዓለም አቀፍ ቅቡልነት ያለው የዲፕሎማሲ ስኬት ማሸጋገር እንደተቻለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።
በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት በተነሱላቸው ጉዳዮች ላይ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም በኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ፣ በጎረቤትና ዓለም አቀፍ ሀገራት፣ የቆንስላ አገልግሎት፣ ለጉዲፈቻ የተሰጡ ህፃናት ያሉበት ሁኔታ፣ ዜጋ ተኮርና ዲጂታል ስኬቶችን በተመለከተ ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮችን አንስተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ በላይ ዓለም አቀፍ ተሰሚነትና የዲፕሎማሲ ስኬቶችን እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ክብር የሚያስጠብቁ ቀጣናዊ፣ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ትብብር ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) የኢትዮጵያን ወቅታዊ የዲፕሎማሲ ክንውን በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ከአብዛኞቹ የቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ መልካም የጉርብትና ግንኙነት አላት ብለዋል።
ኃያላን ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በሚሻኮቱበት ምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል።
የጎረቤት ሀገራትን ግንኙነትም በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በባቡር፣ መንገድና ሌሎች መሠረተ ልማቶች የማስተሳሰር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በማጠናከር የዜጎችን ጥቅምና ክብር የሚያስጠብቁ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም በኪን-ኢትዮጵያ፣ በኢጋድ የስኬታማ ጋዜጠኞች ዕውቅና የኢትዮጵያን ባህልና የልማት እንቅስቃሴ ማስገንዘብ ያስቻሉ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።
በሕገወጥና ደላሎች ተታለው በመካከለኛው ምስራቅ ሳዑዲ አረቢያና ማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የነበሩ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን አስረድተዋል።
ሕጋዊ የስራ ስምምነት በተፈጸመባቸው ሀገራት ለሥራ ስምሪት የተጓዙ ዜጎች መብትና ጥቅማቸው ተጠብቆ የሚሰሩበትን የቆንስላና የዲፕሎማሲ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የረጅም ዓመታት ስትራቴጂካዊ ዕቅድን፣ የትውልድንና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምን ባገናዘበ መልኩ ምላሽ የሚያገኝበት የዲፕሎማሲ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት አጀንዳ ለዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ማስገንዘብ ያስቻሉ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ እንዴት ይፈጸም ወደሚል ዓለም አቀፍ ቅቡልነት ያለው የዲፕሎማሲ ስኬት ማሸጋገር እንደተቻለ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያውያን የትውልድ ጥያቄ የሆነውን የባሕር በር ጉዳይ የትውልድ ጥያቄ መሆኑንም አብራርተዋል።
ይህንን ታሳቢ በማድረግም ከሀገር ውስጥ እስከ መላ ዓለም የሚገኙ ዜጎች በሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በጋራ አጀንዳነት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።