የገጠሩን ማህበረሰብ በመሰረተ ልማት በማገናኘት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የገጠሩን ማህበረሰብ በመሰረተ ልማት በማገናኘት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል
ሆሳዕና፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ የገጠሩን ማህበረሰብ በመሰረተ ልማት በማገናኘት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትኩረት መደረጉን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለፁ፡፡
ሀገራዊ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ የገጠር ቤትና መሰረተ ልማት ንቅናቄ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በዚህ ወቅት እንዳሉት የገጠሩን ማህበረሰብ አኗኗር በማዘመን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የገጠር ቀበሌ ማዕከላት ተመስርተዋል፡፡
ማዕከላቱ ተበታትኖ የሚኖረውን አርሶ አደር በተወሰነ ቦታ በማሰባሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን በመገንባት የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡
የገጠር ቀበሌ ማዕከላቱን ተደራሽነት ለማስፋትና በፕላን ለመምራት የንቅናቄ መድረኩ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕቀፉን ለማሳካት የገጠር ማዕከላቱ ተቀናጅተው በመስራት ግብርናውን የማዘመን፣ የገጠር መሰረተ ልማትን የማሟላትና የገበያ ትስስርን የማጠናከር ዓላማ እንዳላቸው አንስተዋል።
ይህን ለመተግበር ከመድረኩ የሚገኙ ተሞክሮዎችን በመቀመር ለገጠሩ ማህበረሰብ ምቹ አካባቢን ለመፍጠርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
የንቅናቄ መድረኩ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በሀገራዊ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ የገጠር ቤትና መሰረተ ልማትን ተግባራዊ ለማድረግ ማለሙን ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም መንግሥት በከተሞች የዜጎችን የቤት ጥያቄ ለመመለስ ፖሊሲ በማሻሻል ባለሀብቱን በማሳተፍ ጭምር የቤት አቅርቦትን ማሳደጉን አንስተዋል፡፡
በዚህም የከተሞችን ፕላንና የመሰረተ ልማት ተደራሽነት በማስፋት ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊዎችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው፡፡
ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው የንቅናቄ መድረክ በተለያዩ ክልሎች ገጠሩን ትራንስፎርም ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ቀርበው ውይይት ተካሄዶባቸው ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ተመላክቷል፡፡