ቀጥታ፡

በብሔረሰብ አስተዳደሩ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ሰፊ የውሃ አማራጮችና የልማት እድሎች አግኝተናል--ወጣቶች

ሰቆጣ፤ ታህሳስ 21/2018 (ኢዜአ)፡- በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የውሃ አማራጮች በመስፋታቸው በመስኖ ልማት በመሰማራት ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ገለፁ።

የሰቆጣ ከተማ የ2018 የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ በ04 ቀበሌ ቦሹ ተፋሰስ ላይ ተጀምሯል።

በብሔረሰብ አስተዳደሩ የከርሰ ምድርና ገፀ ምድር የውሃ አማራጮችን በማሳደግ ከ700 በላይ ወጣቶች በንብ ማነብ፣ በከብት ማድለብና በአትክልት ልማት ስራ እንዲሰማሩ ማስቻሉም ተመልክቷል።

በወቅቱም ወጣቶቹ፤ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የውሃ አማራጮች በመስፋቱ በመስኖ ልማት ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በከተማው የ04 ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ወጣት ፋንታው ጌታወይ ለኢዜአ እንደገለፀው በአካባቢያቸው የሚገኘውን ቦሹ ተፋሰስ ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ መልሶ እንዲያገግም አድርገዋል።

በእርከን የታገዘው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራው በተፋሰሱ ስር በሚገኙ አካባቢዎች የውሃ ማመንጨት አቅም በመጨመሩ ወጣቶች በመስኖ ልማት እንዲሰማሩ ማስቻሉን ገልጿል።

"እኔ ከአሁን ቀደም ምንም ስራ አልነበረኝም" ያለው ወጣት ፋንታው አሁን ላይ ያለሙት ተፋሰሶች የውሃ አማራጮችን በማስፋታቸው በአትክልት ልማት ስራ ላይ ለመሰማራት መቻላቸውን ገልጿል።

ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አወጣ ቸኮለ በበኩሉ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ድንች እያመረተ መሆኑን ተናግሯል።

ያመረተውን ምርትም ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነቱን በማሳደግ ሃብት እያፈራ መሆኑን ገልጿል።

በየዓመቱ የሚሰሩ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች በአግባቡ ከተጠበቁ ውጤት እንዳለው በቦሹ ተፋሰስ አረጋግጠናል ያለው ደግሞ ወጣት ፋንታው ፀሃዩ ነው።

እያገኘን ያለነውን ጥቅም ዘላቂነት ለማረጋገጥም በዘንድሮው በጋ በሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ግንባር ቀደም ተዋናይ ለመሆን ስራውን መጀመራቸውን አስረድቷል።


 

የሰቆጣ ከተማ ግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሚዛን ጌታወይ በከተማው ዙሪያ በሚገኙ ገጠር ቀበሌዎች የለሙ ተፋሰሶች ለወጣቱ የገቢ ምንጭ እየሆኑ ነው ብለዋል።

የለሙ ተፋሰሶች የአፈር ለምነትን በመጨመር የአርሶ አደሩ ምርታማነት እንዲያድግ ማስቻላቸውን የገለጹት ደግሞ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ ናቸው።

በተጨማሪም የከርሰ ምድርና ገፀ ምድር የውሃ አማራጮችን በማሳደግ ከ700 በላይ ወጣቶች በንብ ማነብ፣ በከብት ማድለብና በአትክልት ልማት ላይ እንዲሰማሩ ማስቻሉን አስረድተዋል።


 

በብሔረሰብ አስተዳደሩ በተያዘው ዓመት በ366 ተፋሰሶች ላይ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ማካሄድ መጀመሩን አስረድተዋል።

እየተሰሩ ያሉ ተፋሰሶችን ዘላቂነት ለማረጋገጥም የተፋሰሶች ህብረት ስራ ማህበራት በማቋቋም የተጠናከረ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲደረግ መሰራቱንም አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም