ቀጥታ፡

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የተያዙ ትልሞች የቡናውን ዘርፍ የበለጠ ውጤታማ የሚያደርጉ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የተያዙ ትልሞች የቡናውን ዘርፍ የበለጠ ውጤታማ የሚያደርጉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

ኢትዮጵያ የግብርናውን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ የተሻሻሉ ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች።

የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ዋነኛ ምንጭ የሆነው ቡናም የዚህ አካል ሲሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታት በቡና ምርትና ምርታማነት ላይ በተከናወኑ ስራዎች ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል።


 

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ዑመር ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከለውጡ ዓመታት በፊት ከ500ሺህ ቶን ጥቂት ከፍ ያለ ቡና እንደሚመረትና ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ብቻ ለውጭ ገበያ ይቀርብ እንደነበር አስታውሰዋል።

የለውጡ መንግስት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብርን ጨምሮ ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማገዝ በወሰዳቸው እርምጃዎች በቡና ምርትና ምርታማነት ላይ የሶስት እጥፍ እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ ግኝት አራት እጥፍ እድገት መመዝገቡ የዘርፉን ሁለንተናዊ ስኬት ያሳያል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ቴክኖሎጂ የላቀ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፣ በቡና እሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ አሰራሮችንም በቴክኖሎጂ የማገዝ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዲጂታል 2030 ስትራቴጂ የተለያዩ ዘርፎችን ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት የመጠቀም እቅድ ይዞ መምጣቱን ነው የገለጹት።

በተለይም የአርሶ አደሩን የገበያ መረጃ እጥረት ለመፍታትና አዳዲስ ዝርያዎችን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የተያዙ ትልሞች ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር ፕሬዝዳንት ሁሴን አምቦ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ቡናን በጥራትና በብዛት ለማምረት ከባህላዊ አሰራር መውጣትና ዘርፉን ማዘመን ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል።

የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ የእያንዳንዱ ቡና አምራች አርሶ አደር ማንነት እንዲለይ በማድረግ የቡና ምርትንና ንግድን ህጋዊና ዘመናዊ ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት።

ለዚህ ማህበሩ በቡና ዘርፍ እሴት ሰንሰለት ውስጥ ለሚገኙ አካላት የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው የተወሰኑ ቡና አምራቾቸ ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በጀመሩት ጥረት የሚታይ ውጤት መገኘቱን አመልክተዋል።

በዲጂታል 2030 ስትራቴጂ በመታገዝ ተሞክሮውን የበለጠ ማስፋት አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።

በአውሮፓ ህብረት የደን ጭፍጨፋ ቁጥጥር ደንብ መሰረት እያንዳንዱ የቡና ምርት ያለበትን ቦታ በሳተላይት ማሳየት የሚያስችል ሥርዓት እንዲዘረጋ ይጠይቃል ነው ያሉት።

ከዚህ አኳያ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ አርሶ አደሩ የተለያዩ ሀገራት የሚያወጧቸውን ህጎች ተረድቶ በዚያ መሰረት እንዲያመርት ዕድል የሚሰጥ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም