ቀጥታ፡

የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማጠናከር የተጀመሩ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚናቸውን ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማጠናከር የተጀመሩ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚናቸውን ሊያጎለብቱ እንደሚገባ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና ሀላፊ ሞገስ ባልቻ ገለጹ።

በ"ዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አባበ ለሚገኙ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስልጠና እየተሰጠ ነው።


 

በስልጠና መርሃ ግብሩ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና ሀላፊ ሞገስ ባልቻ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መንግስት ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው።

ለዚህም ጠንካራ ተቋማት አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለተቋማቱ መጠናከር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድርሻ የላቀ መሆኑን አንስተዋል።

የሀገር ግንባታ ሂደት የሚሳካው በኃይልና በግጭት ሳይሆን፣ ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይትና ምክክር በመፍታትና ለሃሳብ የበላይነት ተገዢ በመሆን ነው ብለዋል።

መሰል የዲሞክራሲ ልምምድ እንዲጎለብት የሲቪል ማህበራት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

መንግሥት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶችና የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መድረክ መመስረቱን ተናግረዋል።

ይሄ መድረክ በአዲስ አበባ ደረጃም መመስረቱን አስታውሰው፤ በዚህ መድረክ ላይም በአዲስ አበባ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልፀዋል።


 

በአዲስ አበባ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ ሚኤሳ ኤሌማ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ስልጠናው በመዲናዋ ያሉ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚናቸውን ይበልጥ ለማጉላት ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመንግሥት እና በድርጅቶች መካከል ይበልጥ ተቀራርቦ ለህዝብ ጥቅም መስራት ሌላው የስልጠናው ዓላማ መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም