የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ መርሃግብር በዲጂታል ስነ ምህዳር ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ መርሃግብር በዲጂታል ስነ ምህዳር ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ያስችላል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ):- የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ መርሃግብር በዲጂታል ስነ-ምህዳር ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችል ክህሎት እየፈጠረላቸው መሆኑን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ገለጹ።
ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት መሰረተ ልማትና አስቻይ ስርዓት ከመዘርጋት በተጨማሪ የዲጂታል ክህሎት ያለው ማህበረሰብ አስፈላጊ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓም የአምስት ሚሊየን ኮደርስ ኢኒሼቲቭን ማስጀመራችው ይታወሳል።
ኢኒሼቲቩ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስና የኢትዮጵያ መንግስታት የሚተገበር ሲሆን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ 5 ሚሊዮን ወጣቶች በኦንላይን የኮዲንግ ስልጠና የሚወስዱበት ነው።
ስልጠናው በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ ዳታ ሳይንስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዳሉት የኮደርስ ስልጠና ዘመኑ የሚጠይቀውን የዲጂታል ክህሎት ለማጎልበት መሰረት የሚሆን ነው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ሲስተም ተማሪ አርሴማ መንግስቱ የኮደርስ ስልጠና ካለክፍያ የቀረበ መሰረታዊ የዲጂታል ክህሎትን ለመገንባት ዕድል መፍጠሩን ተናግራለች።
የኮደርስ ስልጠና ለዲጂታላይዜሽን መፋጠን ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ሰው ስልጠናውን ሊከታተል እንደሚገባ ገልፃለች።
በዩኒቨርሲቲው ሌላኛዋ የኢንፎርሜሽን ሲስተም ተማሪ ፅዮን ምስጋናው በበኩሏ የኮደርስ ስልጠና ለሁሉም ሰው በተመቸ አግባብ የተዘጋጀ ነው ብላለች።
በኮደርስ ስልጠና ያገኘችው መሰረታዊ የዲጂታል ክህሎት ለመደበኛ ትምህርቷ እገዛ እንዳደረገላትም ነው ያስረዳችው።
ስልጠናው ለቴክኖሎጂ አጠቃቀም መመሪያ በሚሆንና ሁሉም ሰው ሊረዳ በሚችለው አግባብ የተዘጋጀ መሆኑን የተናገረችው ደግሞ የኢንፎርሜሽን ሲስተም ተማሪዋ ቤተልሄም ሰለሞን ነች።
የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ተማሪ ገለታ ካፎ እንዳለው ስልጠናው በኮምፒውተርም ሆነ በስልክ ኦንላይን መከታተል የሚቻል ነው።
ተማሪዎች ስልጠናውን በመከታተል የዲጂታል ክህሎታቸውን ማሳደግ አለባቸው ያለው የዩኒቨርሲቲው የትምህርት አመራርና አስተዳደር ተማሪ ዲቃባ ጎንጂ ነው።