ቀጥታ፡

የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና የኢትዮጵያን የንግድና የሎጂስቲክስ ሥርዓት በማቀላጠፍ በኩል ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየታዩበት ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ):- የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና የኢትዮጵያን የንግድና የሎጂስቲክስ ሥርዓት በማቀላጠፍ በኩል ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየታዩበት መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ(ዶ/ር) ገለጹ።

ቀጣናው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ያለውን ሚና ለማሳደግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

ኮርፖሬሽኑ በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና ዙሪያ በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት ግልጽነት ለመፍጠርና ባለሀብቶች በቀጣናው ውስጥ በስፋት እንዲሳተፉ ለማበረታታት ያለመ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።


 

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና ወደ ሙሉ ትግበራ ከገባ ገና አንድ ዓመት ያልሞላው ቢሆንም፣ የሀገሪቱን የንግድና የሎጂስቲክስ ሥርዓት በማቀላጠፍ ረገድ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየታዩበት ይገኛል ብለዋል።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አራት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ምርት በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና በኩል ለማሳለጥ ግብ ተቀምጦ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ቀጣናው ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ብልጽግና ያለውን ሚና ለማሳደግ የመንግሥት ተቋማትና የግል ዘርፉ በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበው የሥራ ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶችም በአፋጣኝ ወደ ሥራ መግባት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነፃ የንግድ ቀጣና ሲሆን፣ ሀገሪቱን ከዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ጋር ለማስተሳሰር የታለመ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

ነጻ የንግድ ቀጣናው የሎጂስቲክስ ወጪን ለመቀነስ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንዲሁም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ አበርክቶ ይጫወታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም