በድሬደዋ የተፋሰስ ልማት የአፈርና የውሃ ሀብትን በማልማት የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በድሬደዋ የተፋሰስ ልማት የአፈርና የውሃ ሀብትን በማልማት የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ እያገዘ ነው
ድሬደዋ፣ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ):- በድሬደዋ የተፋሰስ ልማት የአፈርና የውሃ ሀብትን በማልማት የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ እያገዘ መሆኑን የአስተዳደሩ ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ገለፀ።
በአስተዳደሩ በዘንድሮ የበጋ ወራት በ5ሺህ 550 ሄክታር የተራቆቱ ተፋሰሶች ላይ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራዎች እንደሚካሄድ ተመላክቷል።
በአስተዳደሩ ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና የገጠር መሬት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አሊይ አህመድ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ባለፉት ዓመታት በተራቆቱ ተፋሰሶቸ ላይ በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የምግብ ሉአላዊነት ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጉዞ ስኬታማ እያደረጉ ናቸው።
የተሰሩት የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራዎች ምንጮች እንዲጎለብቱ እና አነስተኛ የመስኖ ልማቶች በአስተዳደሩ የገጠር ቀበሌዎች እንዲስፋፉ አስችለዋል ብለዋል።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎቹ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እና ለእንሰሳት መኖ ልማት ለማግኘት ማገዛቸውን ጠቁመዋል።
ይህም አርሶአደሮች እና አርብቶአደሮች በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን እንዲያረጋግጡ እያስቻለ መሆኑን አቶ አሊይ ተናግረዋል።
በተለይም ወጣቶችና ሴቶች የተፋሰስ ልማቱ ላይ በማህበር ተደራጅተው በመንከባከብና በተፋሰስ ልማቱ በተፈጠሩ አዳዲስ የእርሻ መሬቶችን ወደ ልማት በማሸጋገር ተጠቃሚ መሆናቸውን በመግለፅ።
እነዚህን ውጤቶች በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል በዘንድሮ የበጋ ወራት 5ሺህ 550 ሄክታር የተራቆቱ ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።
ከተፋሰስ ልማቱ በተጨማሪ ስነ ምህዳሩን የሚያጎለብቱና ለቀጣዩ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ስራ መደላድል የሚፈጥሩ ስራዎች እንደሚከናወኑም ገልጸዋል።
በዚህ ወር መጨረሻ በሚጀመረው የተፋሰስ ልማት ላይ ከ37ሺህ 550 በላይ የአስተዳደሩ ነዋሪዎች በልማቱ ላይ ይሳተፋሉ ብለዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለፁት አርሶአደር ሐሰን ያሶ እና አርሶአደር አብዱላሂ ዩሱፍ በበኩላቸው የተፋሰስ ልማቱ በጎርፍ ይታጠብ የነበረውን ለም አፈር ለልማት በማዋል የተሻለ ምርት ለማግኘት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
በተለይም ምንጮች ጎልብተው በመስኖ ልማት መሰማራታቸው የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እንዳስቻላቸው ጠቅሰው ዘንድሮ በሚካሄደው የበጋ ተፋሰስ ልማት ላይ ለመሳተፍ እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል።