የጎንደር ከተማ የዲጂታል አድራሻ ስርዓት በመጪው ጥር ወር ስራ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደር ከተማ የዲጂታል አድራሻ ስርዓት በመጪው ጥር ወር ስራ ይጀምራል
ጎንደር፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ በጎንደር ከተማ የዲጂታል አድራሻ ስርዓትን በመጪው ጥር ወር ስራ ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን የከተማ አስተዳደሩ የስማርት ሲቲ ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ጋር ጥቅምት 2018 ዓም ጎንደር ከተማን የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የፕሮጀክት ስምምነት በተፈረመበት ወቅት ፕሮጀክቱ ጥር ወር 2018 ተጠናቅቆ ወደ ስራ እንደሚገባ መገለጹ ይታወሳል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የስማርት ሲቲ ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ይልቃል ሙሉአለም(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ከስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት የዲጂታል አድራሻ ሰርዓት ትግበራን ለማሳካት ሲሰራ ቆይቷል።
ስርዓቱ መንግስት ከተሞችን ለማዘመን የጀመራቸውን የዲጂታላይዜሽን ስትራቴጂ አጠናክሮ የሚያስቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት ከኢኒስቲትዩቱ ጋር በመተባበር በቴክኖሎጂ የተደገፉ የዲጂታል ዳታዎችን የማሰባሰብና የማደራጀት ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አውስተዋል።
በጂፒኤስና በዲጂታል ካርታ የተደራጀው የዲጂታል የአድራሻ ስርዓት በከተማው መሬት ላይ ያሉ ሀብቶችን፤ መሰረተ ልማቶችን ቤቶችንና የዋና ዋና መንገዶች ቋሚ አድራሻዎችን በቀላሉ ለተጠቃሚው አቅጣጫ የሚያመላክት ነው ብለዋል።
የዲጂታል ቴክኖሎጂውን ወደ ተግባር ማሸጋገር የሚያስችሉ የሳተላይት ምስልና መረጃ መሰብሰብን ጨምሮ ከ60ሺህ በላይ የመንገድና የትራፊክ እንዲሁም የቦታ መረጃ የማደራጀት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡
ከ74ሺህ በላይ ህንጻዎችና መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ 682 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የዲጂታል የመንገድ ኔትወርክ መረጃዎች ተሰብስበው ወደ ሲስተም መግባታቸውንም አረጋግጠዋል፡፡
ስርዓቱ ለዲጂታል ኢኮኖሚው እድገት መፋጠን፤ ለዘመናዊ ከተማ ግንባታ፤ ለቱሪዝም እንዱስትሪ ማደግ፣ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመንና የከተማውን ጸጥታና ደህንነት በቴክኖሎጂ ለመቆጣጠር ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡
ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ፣ የውሃና የቴሌ ኮም የጥገና አገልግሎቶችን ባሉበት ቦታ ሆነው እንዲያገኙና አገልግሎት የሚሰጡ አካላትም በፍጥነት ደርሰው ምላሽ እንዲሰጡ አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የእሳት አደጋ እና ድንገተኛ የአምቡላንስ እርዳታ አገልግሎቶችን ነዋሪዎች በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ የዲጂታል አድራሻ ስርዓቱ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በከተማው የሚገኙ የመንግስት ተቋማት፣ የግል መኖሪያና የንግድ ቤቶችም ዲጂታል መለያ ቁጥር እንደተዘጋጀላቸው ጠቁመው ፕሮጀክቱ ጥር 2018 ዓም ተመርቆ ስራ እንደሚጀመርም ገልጸዋል፡፡
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ኢኒሼቲቭ ውጤት የሆነው የዲጂታል አድራሻ ስርዓት የከተማውን እድገትና ልማት የሚጠቁሙ አዳዲስ መረጃዎች በየሦስት ወሩ ወደ ሲስተም የማስገባት ስራ እንደሚቀጥል ታውቀዋል፡፡
የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ 100 ከተሞችን ተደራሽ የሚያደርግ የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን ጥቅምት 7/2018 ጎንደር ከተማን የዲጂታል አድራሻ ስርዓቱ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት የመግባቢያ ሰነድ በተፈረመበት ወቅት መግለጹ ይታወሳል፡፡
በአማራ ክልል ደብረ ብርሃን እና ኮምቦልቻ ከተሞች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ መሆናቸውንና በደሴና ወልዲያ ከተሞችም ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ መታቀዱን የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላቸው ፀሐይ መናገራቸውም እንዲሁ፡፡
በወቅቱ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እንዳሉት አስተዳደሩ ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት ከኢንስቲትዩቱ ጋር በቅርበት ይሰራል።
ጥር 2018ዓም በከተማው በድምቀት ለሚከበረው የጥምቀት በዓል ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን መናገራቸውም ይታወሳል፡፡