ቀጥታ፡

ለአገራችን ለከፈልነው መስዋዕትነት በመንግሥት እና በህዝብ ተክሰናል - በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡ ቤቶች ባለቤቶች

ድሬደዋ ፣ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፡- ለአገር ለከፈሉት መስዋዕትነት በመንግስትና በህዝብ ትብብር መካሳቸውን በድሬደዋ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡ ቤቶች ባለቤት የሆኑና በቦርድ የተገለሉ የሰራዊት አባላትና ቤተሰቦች ተናገሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በኬንያ ናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲን ጨምሮ የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት  በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ድሬዳዋ ላይ ያስገነቡትን 20 ዘመናዊ ቤቶች በደመቀ ስነ-ስርዓት ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች ማስረከባቸው ይታወሳል።

የቤት ባለቤት ከሆኑት ነዋሪዎች መካከል በቦርድ የተገለሉ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት እና የድሬደዋ አስተዳደር ገጠር ክላስተር አቅመ ደካማ ነዋሪዎች ተጠቃሽ ናቸው።

የቤት ባለቤት ከሆኑት መካከል አስር አለቃ ውብሸት ፈለቀ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለዜጎች ክብር መስዋዕትነት መክፈል የሚያኮራና የዜግነት አኩሪ ኃላፊነት ነው።

አስር አለቃ ውብሸት እንዳሉት፤ ይሄን አኩሪ ተግባር በመወጣት ላይ ሳሉ በደረሰባቸው ጉዳት ከሠራዊቱ በቦርድ ወጥተው ለማህበራዊ ችግር ቢዳረጉም መንግስትና ህዝብ ተቀናጅተው ያደረጉት ድጋፍ ተስፋቸውን አለምልሞታል።

በአደባባይ መካሳቸው ቀጣዩን ህይወት በተስፋ ለመምራት እንደሚያስችላቸውም ገልፀዋል።


 

በቦርድ የወጡት የመቶ አለቃ ተገኔ እናት ወይዘሮ አዘረፈች አባተ እና የመቶ አለቃ ተገኔ ልጅ ተማሪ ፅዮን ተገኔ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው በተስፋ የተሞላ አዲስ የህይወት ምዕራፍ ለመጀመር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የቤት ባለቤት ካደረጓቸው አቅመ ደካማ ወገኖች መካከል የድሬዳዋ የገጠር ክላስተር ነዋሪዎች ይገኙበታል።


 

የጀሎ በሊና ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሳሮ አህመድ ለዓመታት በመኖሪያ ቤት እጦት ይደርስባቸው የነበረው ችግር በመፈታቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን የሚያስተባብረው የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን በበኩሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም የተለያዩ የፌደራል ተቋማት ባሳለፍነው ክረምት በተካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ ያደረጉት ተሳትፎና የፈጠሩት ትስስር በአርዓያነት የሚገለጽ መሆኑን አስታውቋል።


 

በኮሚሽኑ የወጣቶችና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ በሐር አብደላ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በበጎ ፈቃድ የተከናወኑ የልማት ተግባራት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከመፍታት ባሻገር ትስስርና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን እያፀኑ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም