ቀጥታ፡

በምስራቅ ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ የሚለማ 266 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር ተሸፍኗል

አዳማ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ በምስራቅ ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ የሚለማ 266 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለፀ።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አብነት ዘገየ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በዞኑ 11 ወረዳዎች በዘንድሮው የበጋ መስኖ 250ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ለማልማት ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል።

እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ ከእቅድ በላይ 266ሺሀ 700 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን መቻሉን ገልጸዋል።

ልማቱን ከእቅድ በላይ ማከናወን የተቻለው አርሶ አደሩ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጠቃሚ እንደሚያደርገው በማረጋገጡ ነው ብለዋል።

በዞኑ በሚገኙ አብዛኞቹ ወረዳዎች የልማት ስራው በትራክተር በመታገዝ በኩታ-ገጠም የታረሰ ሲሆን የሰብል እንክብካቤ ስራውም ከወዲሁ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።

ልማቱ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃን በመጠቀም እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው በዋናነት ሰባት ወረዳዎችን አቋርጦ የሚሄደውን አዋሽ ወንዝ በመጥለፍ፣ በዘመናዊ መስኖ ፕሮጀክቶችና የጉድጓድ ውሃ በመጠቀም ስራው ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል።

የበጋ ስንዴ ልማት በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች በሚገኙና ውሀ ገብ በሆኑ ቀበሌዎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አስታውሰው በልማቱም ወጣቶችና ሴቶችን ጨምሮ ከ120ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ አውስተዋል።

በአጠቃላይ በበጋ መስኖ ስንዴ ከለማው መሬት 13 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም አቶ አብነት አስታውቀዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ኀብረት ሥራ ኤጀንሲ ኃላፊ አስራት ጌቱ በበኩላቸው በዞኑ ስንዴን ጨምሮ በበጋ መስኖ ለሚለማው አትክልትና ፍራፍሬ ልማት 133ሺህ 457 ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም