ቀጥታ፡

በሳውላ ከተማ እየተከናወኑ ለሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን - ነዋሪዎች  

ሳውላ፤ ታህሳስ 21/2018 (ኢዜአ):- በሳውላ ከተማ እየተከናወኑ ለሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የመሰረተ ልማት ስራ ሳውላን ውብና ለኑሮ ምቹ እያደረጋት መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በዚህም በከተማዋ እየተከናወኑ ለሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ ጊያ ሌላ ቦታ ሲሰራ አይተን የተመኘነው የኮሪደር ልማት በከተማችን መጀመሩ አስደስቶኛል ብለዋል።

የኮሪደር ልማቱ ከዚህ ቀደም የቆሻሻ መጣያ የነበረውን ስፍራ ውብ ሆኖ ወደ መዝናኛነት መቀየሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸው ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። 

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ኩማ ኩሳ በበኩላቸው ሳውላ መልማት ካለባት አንጻር ሳትለማ እንደቆየች አስታውሰው አሁን ላይ በከተማው እየተገነባ ያለው የኮሪደር ልማት ትራንስፖርትን ከማሳለጥ ባሻገር ከተማዋን ውብ ገፅታ እያላበሳት ይገኛል ብለዋል።

ለተጀመሩ የልማት ስራዎችም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡ 


 

ከተማዋን ውብ፣ ፅዱና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት የሳውላ ከተማ ከንቲባ ንጉሴ መኮንን (ዶ/ር) በከተማው በመጀመሪያ ዙር የአንድ ኪሎ ሜትር የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማቱ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገና የብስክሌት መንገድን ጨምሮ የአረንጓዴ መናፈሻ ስፍራ እንዳለው ገልጸዋል።

በመጀመሪያው ዙር በ15 ሚሊዮን ብር የተሰራው የ1 ኪሎ ሜትር የተቀናጀ ኮሪደር ልማት ስራ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ያነሱት ከንቲባው በቀጣይም 2 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው በክልሉ ከሚገኙ 41 የከተማ አስተዳደሮች በ20ዎቹ የኮሪደር ልማት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

በቀጣይ 90 ቀናትም በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የከተማ አስተዳደሮች ወደ ኮሪደር ልማት ስራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም