ቀጥታ፡

የአፍሪካ ዋንጫ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች

የአፍሪካ ዋንጫ በርካታ ክዋክብቶች ደምቀው የታዩበት መድረክ ነው። በሀገራት መካከል ያለው ተቀናቃኝነት፣ አይረሴ ገጠመኞች፣ በደጋፊዎች የተሞሉ ስታዲየሞች እና ሀገራቸውን ለክብር ያበቁ እና ታሪክ የጻፉ ተጫዋቾች በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ታይተዋል። 

የአፍሪካ ዋንጫ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎችም የአህጉሪቷ የእግር ኳስ ታሪክ አካል ነው።

ካሜሮናዊው ኮከብ ሳሙኤል ኢቶ 18 ጎሎችን በውድድር ላይ በማስቆጠር የቀዳሚነት ስፍራን ይዟል።

ኢቶ 10 ጎሎቹን ያስቆጠረው በስድስት የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ ነው። እ.አ.አ በ2006 እና 2008 በተካሄዱ ውድድሮች ላይ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል። ሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ከሜሮን ጋር አንስቷል።


 

ኮትዲቯራዊው ላውረን ፖኩ 14 ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ተጫዋቹ ግቦቹን ያስቆጠረው በሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ ነው።

ፖኩ እ.አ.አ በ1970 በሱዳን አስተናጋጅነት በተካሄደው ሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ላይ አምስት ግቦችን በማስቆጠር በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ በአንድ ጨዋታ በርካታ ጎሎችን ከመረብ ላይ ያሳረፈ ተጫዋች ክብረ ወሰንን ባለቤት ነው።

ናይጄሪያው ራሺድ ያኪኒ በ20 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ 13 ግቦችን በማስቆጠር ቀጣዩ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ያኪኒ እ.አ. በ1994 የተካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ያነሳ ሲሆን የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪም ነበር።

 

ግብጻዊው ሀሰን ኤል-ሻዝሊ በስምንት ጨዋታዎች 12 ግቦችን ከመረብ ጋር አገናኝቷል። ይህም በአንድ ጨዋታ በአማካይ 1 ነጥብ 50 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል እንደ ማለት ነው። ይህም በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ውጤታማው አጥቂዎች ከሚባሉት ተርታ እንዲሰለፍ አድርጎታል።

ኤል-ሻዝሊ በሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች ፍጻሜ ላይ ሀትሪክ የሰራ ብቸኛው ተጫዋች ነው።

ካሜሮናዊው ፓትሪክ ምቦማ፣ ግብጻዊው ሆሳም ሀሰን እና ኮትዲቭራዊው ዲዲየር ድሮግባ በተመሳሳይ 11 ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል’

ፓትሪክ ምቦማ በአፍሪካ ዋንጫ ባደረጋቸው 17 ጨዋታዎች 11 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።


 

ሆሳም ሀሰን እና ዲዲየር ድሮግባ በአፍሪካ ዋንጫ 21 ጨዋታዎችን አድርገው በተመሳሳይ 11 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል። በውድድሩ ላይ ትኩረት ከሚስቡት ጉዳዮች አንዱ ማን ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቃል? የሚለው ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም