ቀጥታ፡

በአፍሪካ ዋንጫ ዩጋንዳ ከናይጄሪያ ቤኒን ከሴኔጋል የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሶስት እና አራት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።

በምድብ ሶስት ዩጋንዳ ከናይጄሪያ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ በፌዝ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ዩጋንዳ በምድቡ ካደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ በማግኘት የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃን ይዛለች።

ተጋጣሚዋ ናይጄሪያ በስድስት ነጥብ ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቷ ይታወቃል።  

የምስራቅ አፍሪካዋ ዩጋንዳ ወደ 16 ውስጥ ለመግባት ያላትን ተስፋ ለማለምለም ያላት ብቸኛ አማራጭ ማሸነፍ ብቻ ነው። ናይጄሪያ ካሸነፈች ምድቧን በመሪነት ታጠናቅቃለች። 

በዚሁ ምድብ በተመሳሳይ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ታንዛንያ ከቱኒዚያ በፕሪንስ ሙላይ አብቭደላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ታንዛንያ በአንድ ነጥብ ሶስተኛ፣ ቱኒዚያ በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል። 

የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ የሆነችው ታንዛንያ ጥሎ ማለፉን ለመቀላቀል ጨዋታውን ማሸነፍ ይጠበቅበታል። በአንጻሩ ቱኒዚያ ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ጥሎ ማለፍ ያስገባታል።

በተያያዘም የምድብ አራት የመጨረሻ መርሃ ግብር ዛሬ ማምሻውን ይደረጋል። ቤኒን ከሴኔጋል ምሽት አራት ሰዓት ላይ በታንጀር ስታዲየም ይጫወታሉ። 

በምድቡ ቤኒን በሶስት ነጥብ ሶስተኛ፣ ሴኔጋል በአራት ነጥብ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዘዋል። 

ቤኒን ማሸነፍ ቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ ያስገባታል። አቻ መውጣትም በሂሳባዊ ስሌት ወደ ጥሎ ማለፍ ሊያስገባት ይችላል።

ተጋጣሚዋ ሴኔጋል ካሸነፈች ወይም አቻ ከወጣች ጥሎ ማለፍ መግባቷን ታረጋግጣለች። ተሸንፋም ጥሩ ሶስተኛ ሆና የማለፍ እድል አላት።

በዚሁ ምድብ ቦትስዋና ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተመሳሳይ ምሽት አራት ሰዓት ላይ በአል መዲና ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ቦትስዋና ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃን ይዛለች። ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። 

የደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቦትስዋና ለማለፍ ያላት ጭላጭል ተስፋ ተጋጣሚዋን በማሸነፍ ላይ የተመሰረተ ነው።

የሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ጥሎ ማለፉን እንድትቀላቀል ያደርጋታል። ተሸንፋም ጥሩ ሶስተኛ ሆና የማለፍ እድል ልታገኝ ትችላለች።

አዘጋጇ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ አልጄሪያ፣ ማሊ፣ ግብጽ እና ደቡብ አፍሪካ እስከ አሁን ጥሎ ማለፍ መግባታቸውን ያረጋገጡ ሀገራት ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም