ቀጥታ፡

በፕሪሚየር ሊጉ አርሰናል ከአስቶንቪላ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2018 (ኢዜአ)፦  የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል።   

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የበዓል ሰሞን ጨዋታዎች መካሄዳቸውን ቀጥለዋል። 

ምሽት 5 ሰዓት ከ15 አርሰናል ከአስቶንቪላ በኤምሬትስ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ትኩረት ስቧል።

አርሰናል በ42 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። አስቶንቪላ በ39 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ሁለቱ ክለቦች በ15ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተገናኝተው አስቶንቪላ 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በዘንድሮው የውድድር ዓመት አርሰናል ጠንካራ ግስጋሴ እያደረገ ነው። በአንጻሩ ጅማሮው ጥሩ ያልነበረው አስቶንቪላ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛል። 

አርሰናል የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ከፍ ያደርጋል። 

ተጋጣሚው አስቶንቪላ ድል ከቀናው ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር በነጥብ እኩል ይሆናል። ጨዋታው በዋንጫ ፉክክሩ ተጽእኖ የሚያሳድር ነው።

የ40 ዓመቱ ዳረን ኢንግላንድ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

በሌሎች መርሃ ግብሮች ቼልሲ ከቦርንማውዝ፣ በርንሌይ ከኒውካስትል ዩናይትድ፣ ኖቲንግሃም ፎረስት ከኤቨርተን እና ዌስትሃም ዩናይትድ ከብራይተን በተመሳሳይ ምሽት 4 ሰዓት ከ30 ላይ ይጫወታሉ።

ማንችስተር ዩናይትድ ከዎልቭስ ምሽት 5 ሰዓት ከ15 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም