ቀጥታ፡

ሲዳማ ቡና የሊጉን መሪነት ዳግም ለመረከብ ከሸገር ከተማ ጋር ይጫወታል 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።  

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና ከሸገር ከተማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ሲዳማ ቡና በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች ስድስቱን ሲያሸንፍ ሽንፈት ያስተናገደው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በቀሪ አራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 14 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያስቆጥር ስድስት ግቦችን አስተናግዷል።

ቡድኑ በ22 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ሸገር ከተማ በበኩሉ በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 11 ጨዋታዎች መካከል ሶስት ጊዜ ድል ሲቀናው አምስት ጊዜ ተሸንፏል። በሶስት ጨዋታዎች ላይ ነጥብ ተጋርቷል። 11 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 13 ግቦችን አስተናግዷል። 

ሸገር ከተማ በ12 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል። 

ሲዳማ ቡና ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ከፋሲል ከነማ  ይረከባል። ሸገር ከተማ ከሶስት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። 

በሌላኛው መርሃ ግብር ሃዋሳ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ከከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሃዋሳ ከተማ በሊጉ 11 ጨዋታዎችን አድርጎ ስድስቱን ሲያሸንፍ በሶስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በ11ዱ ጨዋታዎች 14 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ ዘጠኝ ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ20 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።

በውድድር ዓመቱ ካካሄዳቸው 11 ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን ያሸነፈው ሀድያ ሆሳዕና በበኩሉ አራት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በአራት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 10 ግቦችን ሲያስቆጥር 12 ጎሎችን አስተናግዷል።

ሀድያ ሆሳዕና በ13 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሁለቱ ክለቦች በድል ጉዟቸው ለመቀጠል የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል። 

ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከነጌሌ አርሲ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ድሬዳዋ ከተማ በ16 ነጥብ ዘጠነኛ፣ ነገሌ አርሲ በተመሳሳይ 16 ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ ስምንተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ምድረገነት ሽሬ ከአዳማ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ ምድረገነት ሽሬ በ14 ነጥብ 11ኛ፣ አዳማ ከተማ በ17 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም