እኩል አጋርነትን መፍጠር፤ አዲሱ የአፍሪካ እና ጣልያን የትብብር ምዕራፍ - ኢዜአ አማርኛ
እኩል አጋርነትን መፍጠር፤ አዲሱ የአፍሪካ እና ጣልያን የትብብር ምዕራፍ
የአፍሪካ እና ጣልያን ግንኙነት የጀመረው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ጣልያን እ.አ.አ በ1947 የተፈራረመቻቸው የሰላም ስምምነቶች ቅኝት ግዛት እና የአንድ አካል የፖለቲካ የበላይነት እንዲያከትም አድርጓል።
በድህረ ቅኝ ግዛት ዘመን ጣልያን ከአፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ከቅኝ አገዛዝ የሁለትዮሽ ትስስር ወደ የኢኮኖሚ ትብብር ተሸጋግሯል።
ወቅቱ አፍሪካውያን ሉዓላዊነታቸውን የበለጠ ያረጋገጡበትና ጣልያን ከአፍሪካ ጋር በአዲስ መልክ አጋርነቷን ያደሰችበት ነበር።
ከቅኝ ግዛት በኋላ የአፍሪካ እና የጣልያን ትብብር በባህል መስክ ላይ ብቻ የተገደበ ነው። የንግድ እና የቴክኒክ ትብብሩ ውስን ነበር።
እ.አ.አ ከ1990ዎቹ መግቢያ አንስቶ የአፍሪካ እና ጣልያን ስትራቴጂክ አጋርነት እያበበ የመጣበት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል።
የዲፕሎማሲ ሚሲዮኖች እና የንግድ ቢሮዎች መጨመር እንዲሁም የኢኮኖሚ ትብብር አድማስ መስፋት የትብብሩ መገለጫ ሆኗል።
ዘመናዊው የአፍሪካ እና ጣልያን አጋርነት ከእርዳታ ወደ የጋራ እድገት ምዕራፍ መሸጋገር ችሏል።
የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው የሁለቱን ወገኖች የንግድ እና የኢንቨስትመንት ትብብር አጠናክሯል። የልማት ትብብሩ እርዳታን ከመለገስ ወጥቶ እድገት ተኮር ሆኗል።
ከደህንነት ጋር በተያያዘም የፍልሰት አስተዳደር እና ሽብርተኝነት መዋጋት አንዱ የትብብር መገለጫ ነው።
የጣልያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የአፍሪካ እና ጣልያን የባለፈው ጊዜ የነበሩ ፈተናዎች እውቅና በመስጠት አሁን ላይ የሁለቱን ወገኖች የጋራ ፍላጎት ማስጠበቅ ላይ ትኩረቱን አድርጓል። የፖሊሲው ሰነድ “ ዋጋ እና ክብርን ማዕከል ያደረገ” ዲፕሎማሲ በሚልው እሳቤው ከአፍሪካ ጋር ላለው ወዳጅነት ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጥ አስቀምጧል።
እ.አ.አ በ2024 በሮም የተካሄደው የጣልያን-አፍሪካ ጉባኤ ላይ በቅርብ ጊዜያት ከነበሩ ከፍተኛ መድረኮች መካከል ይጠቀሳል። በጉባኤው ላይ የ45 የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች፣ የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት መሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የልማት አጋሮች ተሳትፈዋል።
ጉባኤው የተካሄደበት ዓመት ጣልያን የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ሊቀ መንበር የነበረችበት ወቅት ሲሆን ጣልያን ከአፍሪካ ጋር ያላትን ትብብር ማጠናከር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ አንኳር ትኩረት ሆኗል።
የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በወቅቱ ጉባኤውን የአፍሪካ እና ጣልያን ትብብርን በአዲስ መልክ የበየነና ትብብሩ እኩል በቆሙ ወገኖች መካከል ያለ ትስስር እንደሆነ አንስተዋል።
ሜሎኒ የሰጪ እና ተቀባይ ዘመን እንዳበቃና የጋራ እድገት እና የጋራ ፍላጎት ላይ የተመረኮዘ ግንኙነት አዲሱ የትብብር ምዕራፍ እንደሆነም ተናግረዋል።
በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር የነበሩት ሙሳ ፋቂ ማህማት የጣልያንን አዲሱን የፖሊሲ ለውጥ ያደነቁ ሲሆን አፍሪካ ከቃል ባለፈ እውነተኛ አጋርነትን ትፈልጋለች ብለዋል።
የፖሊሲ ሽግግሩ ፍትሃዊነትን ያረጋገጠ እና እኩልነትን መሰረት ያደረገ ዓለም መፍጠርን ያማከለ መሆን እንዳለበትም አንስተዋል።
ጣልያን የገባቻቸውን ቃሎች ወደ ተግባር መቀየር አለባት ሲሉም ማህማት ተናግረው ነበር።
በጉባኤው ላይ ይፋ ከተደረጉ ቁልፍ ማዕቀፎች አንዱ የማቴይ እቅድ (The Mattei Plan) ይገኝበታል።
የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ይፋ ያደረጉት የማቴይ ፕላን ጣልያን ከአፍሪካ ጋር ያላት የኢኮኖሚ እና የልማት ትብብር ማጠናክርን ያለመ ነው። የ5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዩሮ የስትራቴጂክ ማዕቀፉ በጣልያኑ የብሄራዊ የዘይት እና ነዳጅ ኩባንያ መስራች ኤነሪኮ ማቴይ የተሰየመ ነው።
ኩባንያው ከአፍሪካ ጋር ከአጭር ጊዜ እርዳታ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ትብብርን በማስቀደም እየሰራ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
የአፍሪካን የኢኮኖሚ እድገት መደገፍ፣ የስራ እድሎችን ማስፋት፣ አፍሪካን የአውሮፓ የኢነርጂ አቅራቢ አጋር የማድረግ ስራን ማስተዋወቅ፣ ለአፍሪካውያን የኢኮኖሚ ችግሮች መፍትሄ በመስጠት ኢ-መደበኛ ፍልሰትን ከምንጩ ማድረቅ እንዲሁም ከበጎ አድራጎት የተላቀቀ የጋራ ተጠቃሚነት እና ትብብርን መፍጠር የእቅዱ አበይት አላማዎች ናቸው ።
ለአራት ዓመታት የሚቆየው የማቴይ እቅድ በአፍሪካውያን በበጎ መልኩ የታየ ሲሆን እቅዱ ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ተነስቷል።
እ.አ.አ በ2023 የአፍሪካ እና የጣልያን የንግድ ልውውጥ 59 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዩሮ መድረሱን ይፋዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። የንግድ ልውውጡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
የአፍሪካ ሀገራት በዋናነት የተፈጥሮ ጋዝ፣ ድፍድፍ ነዳጅ፣ የብረታ ብረት እና ማዕድናት ምርቶች እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ምርቶች የሆኑ ጥሬ እቃዎችን ወደ ጣልያን ይልካሉ።
ጣልያን የኢንዱስትሪ ማሽን እና መሳሪያ፣ እሴት የተጨመረባቸው እቃዎች እና የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች እንዲሁም የኤሌክትሪክ እቃዎች ወደ አፍሪካ ከምትላካቸው ምርቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
አጠቃላይ የንግድ ምጣኔው ሲታይ ጣልያን በገቢ አብዛኛውን ድርሻ ትይዛለች።
ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ተፈጥሮ ሀብት፣ ኢነርጂ፣ መሰረተ ልማት፣ ትራንስፖርት፣ ትምህርት፣ ምርምር፣ ጤና፣ ቴክኖሎጂ፣ የፍልሰት አስተዳደር፣ ደህንነት እና አስተዳደር ከአፍሪካ እና ጣልያን የትብብር መስኮች መካከል ይገኙበታል።
የ2026 የአፍሪካ-ጣልያን ጉባኤ በየካቲት ወር አጋማሽ 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ እና የአህጉሪቷ መዲና ናት። ይህም ጉባኤውን የአፍሪካ ዋንኛ የዲፕሎማሲ አጀንዳ ያደርገዋል።
ኢትዮጵያ በታሪክ በፓን አፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ የመሪነት ሚና ያላት ሀገር ናት። በአሁኑ ሰዓትም በርካታ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን እያዘጋጀች ትገኛለች።
የሁለቱን ወገኖች አጋርነት የበለጠ ያጠናክረዋል ተብሎ ይጠበቃል። የማቴይ እቅድ ትግበራ፣ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብር፣ የአፍሪካን ተሰሚነት መጨመር፣ ፍልሰትን ጨምሮ በጋራ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ አቋም መያዝ፣ የአጋርነት እና የመግባቢያ ስምምነቶች የአፍሪካ-ጣልያን ጉባኤው ውጤቶች ናቸው።
የአፍሪካ-ጣልያን ጉባኤ ካለፈው ታሪካዊ ግንኙነቶች ፣ እያደገ ከመጣው የኢኮኖሚ ትብብር እና የጋራ ፈተናዎችን የመፍታት ቁርጠኝነት አኳያ በአፍሪካ እና በጣልያን መካከል አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት እንደሆነ ታምኖበታል።
የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ የሚደረገው ጉባኤ አፍሪካ መር አጋርነት ለመፍጠር እና የአፍሪካን ተሰማኒነት ለመጨመር መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ነው።