ደቡብ አፍሪካ ጥሎ ማለፉን ተቀላቀለች - ኢዜአ አማርኛ
ደቡብ አፍሪካ ጥሎ ማለፉን ተቀላቀለች
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሁለት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ማምሻውን ተደርገዋል።
በማራካሽ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ ዚምባቡዌን 3 ለ 2 አሸንፋለች።
ሺፓንግ ሞሬሚ እና ላይል ፎስተር በጨዋታ፣ ኦስዊን አፖሊስ በፍጹም ቅጣት ምት የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ታዋንዳ ማስዋንሃይስ እና የደቡብ አፍሪካው ኦውብሬይ ማፖሳ ሞዲባ በራሱ ላይ ለዚምባቡዌ ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
በጨዋታው ላይ ደቡብ አፍሪካ ብልጫ ወስዳ ብትጫወትም ከዚምባቡዌ ጠንካራ ፈተና ገጥሟታል።
ውጤቱን ተከትሎ ደቡብ አፍሪካ በስድስት ነጥብ በምድብ ሁለት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ለጥሎ ማለፍ ማለፏን አረጋግጣለች።
ዚምባቡዌ በአንድ ነጥብ አራተኛ ደረጃን በመያዝ ከውድድሩ ውጭ ሆናለች።
በተመሳሳይ በዚሁ ምድብ አንጎላ እና ግብጽ ማምሻውን በአጋዲር ስታዲየም ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
አስቀድሞ ወደ ጥሎ ማለፍ የገባችው ግብጽ በሰባት ነጥብ ምድቡን በመሪነት አጠናቃለች።
በአንጻሩ አንጎላ በሁለት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ከውድድሩ ተሰናብታለች።