ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከቻይና፣ ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካ ጋር በፍትህ ዘርፍ ያደረገቻቸው ስምምነቶች ከሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክራሉ

አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከቻይና፣ ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካ ጋር በፍትህ ዘርፍ ላይ ያደረገቻቸው ስምምነቶች ከሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግሥቱ ገለጹ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ ለተመሩለት አራት የተለያዩ የስምምነት ማጸደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ የአስረጂ መድረክ አካሂዷል።


 

የመጀመሪያው በኢትዮጵያ መንግስት እና በህዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና መንግስት መካከል የተደረገውን ፍርደኞችን የማስተላለፍ ስምምነት ነው።

ሁለተኛው በኢትዮጵያ መንግስት እና በህዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የተደረገውን ለወንጀል ጉዳዮች የጋራ የህግ ትብብር ስምምነት ነው።

ሶስተኛው በኢትዮጵያ መንግስት እና የብራዚል ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የተደረገውን ፍርደኞችን ማስተላለፍና አራተኛው የኢትዮጵያና የደቡብ አፍሪካ በወንጀል ጉዳይ የሚፈልጉ ሰዎችን የአሳልፎ መስጠት ስምምነት ረቂቅ አዋጅን ነው።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ማዕከል ባለሙያዎች በቀረቡ የስምምነት ማጸደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ጥያቄ እና አስተያየት ሰጥተዋል።

በስምምነቱ መሰረት ፍርደኞችን አሳልፎ በመስጠት ረገድ ለሚደረገው የሁለትዮሽ ትብብር ጠንካራ የህግ ማዕቀፍን የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም ስምምነቶቹ በፍትህ ዘርፉ ላይ የሚያመጣው አስተዋጽኦ እንዴት ይታያል? ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡


 

በተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ላይ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ፤ ስምምነቶቹ ሀገራቱ ያላቸውን ግንኙነት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የስምምነቱ ዓላማ በህግ ጉዳይ ላይ ሀገራቱ ያላቸውን ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን ጠቁመው፤ በፍትህ ዘርፉ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

በሀገራቱ መካከል ያለውን ስትራቴጂክ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን ጠቅሰው፤ ምክር ቤቱ ስምምነቱን በአጭር ጊዜ ውሰጥ እንዲያጸድቀው ጠይቀዋል።


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ ስምምነቱ በሀገራቱ መካከል ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

ለፍትህ ስርዓቱ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸው፤ ከሀገር ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚያያዝ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ስምምነት መሆኑን አመልክተዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግሥቱ ስምምነቱ የዲፕሎማሲው መስክ እያደገ መምጣቱን ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ታራሚዎችን ከመቀባበል ባለፈ በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም