ቀጥታ፡

በክልሉ ሰላምን ጠብቆ በማዝለቅ ለልማት ምቹ ሁኔታ የመፍጠሩ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል

ባሕር ዳር፤ ታሕሳስ 20/2018(ኢዜአ)፡-  በአማራ ክልል  የሰፈነውን  ሰላም  ጠብቆ  በማዝለቅ ለልማት ምቹ ሁኔታ የመፍጠሩ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።   

የክልሉ ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር  አስቻለ አላምሬ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ፤ በክልሉ ሰላምን በማፅናት  ልማትን ለማፋጠን  በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የሚሊሻና የሰላም አስከባሪዎች  ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ሰላምን ከማስከበራቸው ጎን ለጎን በልማት ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ  ውጤታማ ሥራ ሲያከናውኑ እንደቆዩ አንስተዋል።

ጠንካራ የሕግ ማስክበር ስራ በማከናወን  ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል።

ተግባሩን በማጠናከርም  የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  ትኩረትመሰጠቱን ገልጸው፤ በተለይም የክልሉ የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ዕቅድ ውጤታማ እንዲሆን  በጠንካራ አደረጃጀት ሰላም ማስፈን  ላይ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም የተቋሙን አደረጃጀት ቀደም ሲል ከነበረበት የጽሕፈት ቤት ደረጃ ወደ ኮሚሽንነት መሸጋገሩን  አንስተው፤ የሕግ ማስከበር ሥራውን በላቀ  ብቃትና ቁርጠኝነት  እየተመራ መሆኑን አንስተዋል።

የሰላም አማራጭን በመከተል ባለፉት ጊዜያት  የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶ ሥልጠና ተሰጥቷቸው   ወደ ማህበረሰቡ እየተቀላቀሉ መሆኑን አብራርተዋል።

የቀሩ ታጣቂዎች   ከጥፋታቸው ተመልሰው  የበደሉትን ሕዝብ እንዲክሱ አሁንም መንግስት በሆደ ሰፊነት  የሰላም በሩ ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል።

የሰላም አማራጩን ባልተቀበሉት ላይ የሚወሰደው    እርምጃ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ  መቀጠሉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም