ቀጥታ፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው

ቦንጋ፣ ታህሳስ 20/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የህዝብን ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የተለያዩ ክልሎች አፈ ጉባኤዎች ተናገሩ።

የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች አፈ ጉባኤዎች ፎረም፤ በካፋ ዞን ጥንታዊ የካፋ ነገስታት መናገሻ ’’ቦንጌ ሸምበቶ’’፣ የካፋ ባህል ማዕከል እንዲሁም በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እየተከናወኑ ያሉ የግብርና፣ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችና የውሽውሽ ሻይ ልማት ጎብኝተዋል። 


 

ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አለማየሁ ባውዲ፤ በክልሉ በሁሉም መስክ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ትልቅ ተስፋ የተሰነቀባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ እምቅ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ሃብቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ለዘርፉ ልማት ትኩረት በመስጠት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የተጀመረው ስራ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።


 

የሀረሪ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ሱልጣን አብዱሰላም፤ በጉብኝቱ ጥሩ ልምድ የቀሰሙባቸው ተሞክሮዎች መኖራቸውን አንስተው በድምሩ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጨፌ ኦሮምያ ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሰአዳ አብዱረህማን፤ ሃብቶችን በማልማት ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጥሩ ማሳያዎች መኖራቸውን አንስተው በጉብኝቱ የተመለከቷቸው የተለያዩ የልማት ስራዎችም ይህንኑ የሚያረጋግጡ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በግብርና እና አካባቢ ጥበቃ ላይ እየሰራ ያለዉ ስራ አስደናቂ መሆኑን አንስተው የውሽውሽ ሻይ ልማት ስራም ለበርካቶች የስራ እድል የፈጠረ ሆኗል ብለዋል። 

በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን በጉብኝቱ መመልከታቸውን አፈ ጉባኤዎቹ ተናግረዋል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት  ዋና አፈ ጉባኤ ወንድሙ ኩርታ፤ በካፋ ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲሁም ባህላዊና ታሪካዊ ስፍራዎች በክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች  አፈጉባኤዎች ፎረም ታዳሚዎች መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።

በጉብኝቱ የተሞከሮ ልውውጥ ከማድረግ በተጨማሪ ለቀጣይ የልማት ስራዎች ጥሩ ግብአት የተገኘበት አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች አፈ ጉባኤዎች ፎረም አባላት በነገው እለትም በሚዛን አማን ከተማ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም