ስታርታፖች ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስኬት ገንቢ ሚና ይኖራቸዋል - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
ስታርታፖች ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስኬት ገንቢ ሚና ይኖራቸዋል - ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ ስታርታፖች የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትንና እኩልነትን በማረጋገጥ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስኬት ገንቢ ሚና እንደሚኖራቸው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴሩ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ውጤቶችና በ2030 ስትራቴጂ የትኩረት መስኮች ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉቀን ቀሬ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት መሰረት ጥሏል፡፡
የስትራቴጂው ስኬት የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማትን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ስታርታፖች የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትና እኩልነትን በማረጋገጥ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እና ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስኬት ገንቢ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡
ስትራቴጂው አሁን ላሉት ስታርታፖች መሰረት መጣሉንም ነው ጨምረው የተናገሩት።
ስታርታፖቹ የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን ማድረግ የሚያስችሉ በዲጂታል የበቃ የሰው ኃይል ማፍራታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ 5 ሚሊየን ኮደርስ ስልጠና ሚሊዮነኖች ስታርታፖችን ለመፍጠር ግብዓት የሚሆኑበት አስቻይ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተገበረችው የስታርታፕ አዋጅ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን እንደሚስብ የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኢኖቬሽን ማዕከል ማድረግ ያስችላል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በርካታ ስታርታፖችን በማፍራት የአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሳደግ እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡
ስታርታፖች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ ጥራትና ፍጥነትን በማሻሻል ሁሉን አሳታፊ ለውጥ እንዲያስመዘግቡ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉቀን ቀሬ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የምንገነባት ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘች እንድትሆን ማስቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሀገራዊ ማንነትና እሴትን መሰረት ያደረገ አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ መሰረተ ልማት ግንባታን ማሳለጥ ያስችላል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች ቴክኖሎጂን እንደ ግብዓት የመጠቀም ባህልን ማሳደግ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡