ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የሳይበር ደህንነትን በማጠናከር የዳታ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ያስችላል -ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የሳይበር ደህንነትን በማጠናከር የዳታ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ያስችላል -ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የሳይበር ደህንነትን በማጠናከር የዳታ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ውጤቶችና በ2030 ስትራቴጂ የትኩረት መስኮች ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በፊት የዲጂታል ክፍያ ሥነ ምህዳር አልተፈጠረም አልያም በጅምር ላይ ነበር፡፡
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የክፍያ ሥርዓቱን በማዘመን በኢኮኖሚ ስርዓቱ ላይ ጉልህ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡
በግብይት ሥርዓቱ ቀልጣፋና ግልጽነት ያለው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን በመጠቀም በዲጂታል ኢኮኖሚ ውጤት መለኪያዎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
ይህም ለገንዘብ ህትመት የሚወጣውን የሀብት ብክነት በማስቀረት የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ወደፊት እንዲራመድ አድርጓል ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በማውጣት፣ የኢንተርኔት ተደራሽነትና ትስስርን በማጠናከር የዲጂታል መሰረተ ልማትን በማሳለጥ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግርን ለመፍጠር የዲጂታል ክህሎት የታጠቀ ዜጋ መፍጠር ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ባለፉት ዓመታት የመንግሥት ተቋማት በዲጂታል ክህሎት ልማት ሰፊ ሥራ መስራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም የዲጂታል ክህሎትና ግንዛቤን ለማሳደግ በ2016 ዓ.ም የ5 ሚሊየን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ስልጠና በመጀመር 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎችን በመመዝገብ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎችን ዓለም አቀፍ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ሰርተፊኬቱን ያገኙ ዜጎች እውቀትና ክህሎታቸውን በመሸጥ አልያም ስታርት አፖችን በመፍጠር ለሀገር የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገት ገንቢ ሚና እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ካለፈው የአምስት ዓመት ስትራቴጂ በጎ ልምዶችን በመውሰድ የተቀረጸ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የሳይበር ደህንነትን በማጠናከር የዳታ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዘመናዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓትን ለማንበር የዳታ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በስትራቴጂው ዘመናዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከግሉ ዘርፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አረጋገጠዋል፡፡