የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ ነው
ቴፒ፤ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የምርምርና ብዜት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።
ማዕከሉ በሸካ ዞን ለመጀመሪያ ጊዜ በአርሶ አደሮች ያላመደውን "መልካም" የተሰኘ የማሽላ ዝርያ ለተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት አስጎብኝቷል።
የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሰብል ምርምርና ብዜት ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የማዕከሉ ዳይሬክተር ደረጀ ቱሉ(ዶ/ር) ገልጸዋል።
በዚህም በሸካ ዞን የኪ ወረዳ ለመጀመሪያ ጊዜ የለማው "መልካም" የተሰኘ የማሽላ ዝርያ ምርታማነትን የሚያሳድግ ጥሩ የምርምር ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።
የምርምር ማዕከሉ የማሽላ ዝርያን ከማሻሻል በተጓዳኝ ሌሎች የሰብል ምርምርና ብዜት ላይ በመስራት የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጥረት እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።
የማዕከሉ ሰብል ምርምር ሥራ ሂደት አስተባባሪና ተመራማሪ ሸሀሚል አሎ፤ "መልካም" የተሰኘው የማሽላ ዝርያ በሔክታር እስከ 45 ኩንታል ምርት የሚገኝበት መሆኑን አንስተው ድርቅና በሽታን መቋቋም የሚችል መሆኑን ተናግረዋል።
የሸካ ዞን ግብርና፣ ደን አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ መምሪያ የሰብል ግብርና ባለሞያ አለሚቱ ካሳ፤ የተላመደው የማሽላ ዝርያ ከአካባቢው ሥነ ምህዳር ጋር ተሰማሚና ምርታማነቱም የተረጋገጠ በመሆኑ አርሶ አደሮች በስፋት እንዲጠቀሙት ይደረጋል ብለዋል።
"መልካም" የተሰኘ የማሽላ ዘር በማሳቸው ያለሙት አርሶ አደር ታምራት እረና አዲሱ ዝርያ ከቀደመው የአካባቢ ዝርያ በፍጥነት ለምርት እንደሚደርስ ተናግረዋል።
በሦስት ወር ምርት የሚሰጠው ይህን ዝርያን በቀጣይ በስፋት ለማምረት ማቀዳቸውን አክለዋል።
በአርሶ አደር ታምራት ማሳ የለማውን የማሽላ ሰብል በማየት ዘር ተቀብሎ ለማልማት መወሰናቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የአካባቢው አርሶ አደር ጉዲሳ ቶልቻ ናቸው።
የምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አሁን የተመለከቱት ማሽላ እና ያገኙት ልምድን ለመተግበር ማቀዳቸውን ገልጸዋል፡፡
የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል በብሔራዊ ደረጃ ቅመማቅመምን ከማስተባበር ባሻገር ስንዴን ጨምሮ ሌሎች ለአካባቢው ተስማሚ የሰብል አይነቶች ላይ ምርምር በማድረግ የብዜትና ማስፋፊያ ሥራ እያከናወነ ነው።