ዘላቂ ሰላም ከማስፈን በተጓዳኝ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል -የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ ሰላም ከማስፈን በተጓዳኝ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል -የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)
ባህርዳር፤ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ከማስፈን በተጓዳኝ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለጹ።
በክልሉ የመሰረተ ልማት ክላስተር የ5 ወራት የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ በባህርዳር ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)፤ ከምንም በላይ በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር ሂደት መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም በሁሉም አካባቢዎች ሰላምን የማጽናትና የልማት ስራዎችን የማስቀጠል ስራ በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በፌዴራልና በክልሉ መንግስት በጀት በተለያዩ አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች በጥራትና በፍጥነት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ጥራታቸው ተጠብቆ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች ስለመኖራቸውም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው ባለፉት አምስት ወራት 389 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ለመገንባት ታቅዶ ከ70 በመቶ በላይ መፈጸም መቻሉን አስረድተዋል።
በጥገና በኩልም ሰባት ሺህ 100 ኪሎ ሜትር መንገድ በመጠገን ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን አስረድተዋል።
የክልሉን ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ መሰራቱን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ዳኝነት ፈንታ (ዶ/ር) ናቸው።
ባለፉት አምስት ወራትም በጥናትና ዲዛይን የሚገነቡ ፕሮጀክቶችን በመለየት፣ በጨረታና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በማተኮር መሰራቱንም አስረድተዋል።
በክላስተሩ የእቅድ አፈፃፀም ግምገማው ላይ የክልሉ ባለድርሻ ተቋማትና የፌደራል መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።