ቀጥታ፡

በክልሉ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የባለድርሻ አካላት ትብብር ይጠናከራል

ሮቤ፣ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል  የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የባለድርሻ አካላት ትብብር እንደሚጠናከር የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።

ከባሌና ምሥራቅ ባሌ ዞን የተውጣጡ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የኤች አይ ቪ/ኤድስ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በሮቤ ከተማ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከል ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ጉሻ በለኮ እንዳሉት በክልሉ የኤች አይ ቪ/ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የምርመራ ስራዎች፣ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኙ ወገኖች መድኃኒት እንዲያገኙ ማድረግን ጨምሮ ግንዛቤ የማሳደግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ቀደም ባሉት ዓመታት የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭትን በመከላከሉ ረገድ ውጤት የተገኘ ቢሆንም፤ አሁን ላይ በተፈጠረው መዘናጋት የበሽታው ስርጭት እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በአሁኑ ወቅት የክልሉ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት 0 ነጥብ 03 በመቶ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ኃላፊው በቀጣይ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት የመከላከል ስራው ይጠናከራል ብለዋል።

ስራውን ውጤታማ በማድረግ ሂደት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር እንደሚጠናከር አስረድተዋል።


 

የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ስርጭት ለመግታት የተጠናከረ የህዝብ ንቅናቄ ይከናወናል ያሉት ደግሞ የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ዲኖ አሚን ናቸው።

በተለይም ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት ግንዛቤ የማሳደግ ስራ በትኩረት ይከናወናል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም