የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የኢንዱስትሪ የምርት ተወዳዳሪነትን ለማሳለጥ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የኢንዱስትሪ የምርት ተወዳዳሪነትን ለማሳለጥ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል
አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የአምራች ኢንዱስትሪ የምርት ጥራትና ተወዳዳሪነትን ለማሳለጥ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ማጠናቀቂያና የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ማስጀመሪያ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱ ይታወቃል።
በዚሁ ወቅትም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል ዕድል መፍጠር፣ የዜጎችና ተቋማትን መተማመን ማጎልበት ቁልፍ ትልሞች መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ቁልፍ ትልሞችም የሕዝብ ዲጂታል መሠረተ ልማቶችን በማስፋት የዜጎችን የዕለት ከዕለት ኑሮ በሰው ተኮር ዲጂታል ሥርዓት ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መነሻነት የአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነትን ማዘመን የሚያስችል መሰረት ተጥሏል ብለዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም በዘመናዊ የቴክኖሎጂ ሥርዓት የታገዘ ተወዳዳሪ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት አቅም ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አንስተዋል።
በቀጣይም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መነሻነት በኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ ከባቢ ውስጥ ምቹ የዲጂታላይዜሽን ምኅዳር ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የዲጂታላይዜሽን ሽግግር የኢንዱስትሪ ዕድገትን በማሳለጥ የምርት ጥራትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማስጠበቅ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማሳለጥ የማይተካ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ያስመዘገበውን እመርታዊ ዕድገት ለማስቀጠልም የዲጂታላይዜሽን መሰረተ ልማት ግንባታ ትኩረት እንደተሰጠው አብራርተዋል።
በዲጂታል ሥርዓት የተመዘገቡ ውጤቶች በአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት፣ የገበያ ትስስር፣ የመረጃ አያያዝና የምርት ጥራትን በማስጠበቅ ወሳኝ ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ቁልፍ ትልሞች የአምራች ኢንዱስትሪ የዲጂታል መሠረተ ልማትና የምርታማነት አቅም ለማሻሻል ገንቢ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልጸዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ የገበያ አቅርቦት ትስስርና የግብዓት አቅርቦትን ለማሳለጥም ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አንስተዋል።