ቀጥታ፡

“ጥርን በባሕር ዳር" ሁነቶች የከተማዋን የቱሪዝም መስሕቦች ይበልጥ በሚያስተዋውቁ ዝግጅቶች ይከናወናሉ

ባሕር ዳር፤ ታሕሣሥ 20/2018(ኢዜአ)፡- “ጥርን በባሕር ዳር” ሁነቶች የከተማዋን የቱሪዝም መስሕቦች ይበልጥ በሚያስተዋውቁ ዝግጅቶች እንደሚከናወኑ የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ ጋሻው እንዳለው ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በየዓመቱ ሲከናወኑ የቆዩት "ጥርን በባሕርዳር" ሁነቶች ከጎንደር የጥምቀት እና ከላሊበላ ገና በዓላት ጋር በማስተሳሰር የቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር አስችሏል።

ዘንድሮም ይህንኑ ተግባር በማጠናከር የብስክሌት እና የጀልባ ሽርሽር፣ የታንኳ ቀዘፋ ውድድር፣ የባሕልና ኪነ-ጥበባት ፌስቲቫልን ጨምሮ ከ20 ያላነሱ ሁነቶች ይከወናሉ ብለዋል።

የዚሁ አካል የሆነው የባሕልና ኪነ-ጥበባት ፌስቲቫል ከታኅሣሥ 25/2018ዓ.ም ጀምሮ የባሕርዳርን የብዝሀ ባሕላዊ እሴቶች የማስተዋወቅ መርሀ ግብር እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

መርሀ ግብሩን በማስቀጠል የመጽሐፍ አውደ ርዕይ፣ የገና ጨዋታ እና ሌሎች ሁነቶች እንደሚከናወኑም አስረድተዋል።

በተለይም ጥር 3 በሚካሄደው የብስክሌት ሽርሽር የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገጽታ ለመገንባት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ማሳየት የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

የጀልባ ሽርሽር እና የታንኳ ቀዘፋ ውድድር ጥር 6 እና 14 በቅደም ተከተል እንደሚካሄዱ ጠቅሰው፤ በተለይ የታንኳ ቀዘፋ ውድድሩ ጎብኚዎች በየዓመቱ በጉጉት የሚጠብቁት እየሆነ መምጣቱንና ሁነቶቹ ጥር 30 በቁንጅና ውድድር እንደሚጠናቀቁ አስታውቀዋል።

ሁነቶቹ የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ሕብረተሰቡን ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ አቢይና ንኡሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለመደው የእንግዳ አቀባበል ከተማዋንና አካባቢውን ለማስጎብኘት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በቅንጅት እየተከናወኑ መሆኑን አመላክተዋል።

አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንግዶችን በተገቢው እንዲያስተናግዱ ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባር መከናወኑንም አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም