ወንድማማቾች በአፍሪካ ዋንጫ - ኢዜአ አማርኛ
ወንድማማቾች በአፍሪካ ዋንጫ
የአፍሪካ ዋንጫ መልከ ብዙ ውድድር ነው። የሀገራት ተቀናቃኝነት፣ ታሪካዊ ገድሎች፣ አይረሴ የተጫዋቾች የግል ብቃት፣ ጨዋታ ወሳኝ ግቦች እና ዋንጫን ከፍ አድርጎ የማንሳት የኩራት እና የሀገር ፍቅር ስሜት መገለጫዎቹ ናቸው። ከሚቆጠሩ ግቦች እና ዋንጫዎች ባለፈ ቤተሰባዊ ገጽታ ያለው ነው።
የአፍሪካ ዋንጫ በርካታ ወንድማማች ተጫዋቾች በአንድ ሀገር ማልያ ሲጫወቱ የተመለከትንባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው። በአህጉራዊው መድረክ የ68 ዓመታት ጉዞ አብረው የተጫወቱ ወንድማቾች በዚሁ ጽሁፍ እንመለከታለን።
1. ኢታሎ እና ሉቺያኖ ቫሳሎ (ኢትዮጵያ)
ኢታሎ ቫሳሎ እና ሉቺያኖ ቫሳሎ በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወቱ ወንድማማቾች መሆናቸውን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1962 ባዘጋጀችው ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የቫሳሎ ወንድማማቾች አንድ ላይ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫውተዋል። ሉቺያኖ በውድድሩ ላይ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ከግብጹ ባደዊ አብድል ፈታህ ጋር በጋራ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል።
ሉቺያኖ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠ ሲሆን ይህም በውድድሩ ታሪክ የኮከብ ተጫዋችነትን ሽልማት ያገኘ የመጀመሪያው ተጫዋች እንዲሆን አስችሎታል። ኢትዮጵያ በወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫን ማንሳቷ የሚታወስ ነው።
2. ሆሳም እና ኢብራሂም ሀሰን (ግብጽ)
ሆሳም ሀሰን እና ኢብራሂም ሀሰን በአፍሪካ ዋንጫው ስኬታማ የሚባሉ ወንድማማች ተጫዋቾች ናቸው። እ.አ.አ በ1986 ግብጽ ያስተናገደችውን 15ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እና እ.አ.አ በ1998 በቡርኪናፋሶ የተካሄደውን 21ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ግብጽ ስታነሳ የቡድኑ አባላት ነበሩ።
ወንድማማቾቹ የአፍሪካ ዋንጫን ሁለት ጊዜ በማንሳት ባለ ክብረ ወሰን ናቸው።
የ59 ዓመቱ ሆሳም ሀሰን በአሁኑ ሰዓት የግብጽ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ነው። በተጫዋችነቱ በ177 ጨዋታዎች 69 ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የምንጊዜውም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው።
3. አልበርት ባዋንጋ እና ሮበርት ካዛዲ (ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ)
ሁለቱ ወንድማማቾች ግብጽ እ.አ.አ በ1974 ባዘጋጀችው ዘጠነኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በጋራ ተሰልፈዋል።
በወቅቱ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዛምቢያን በማሸነፍ ዋንጫውን ስታነሳ የታሪካዊው ድል አካል ነበሩ።
4. አንድሬ ካና ቢይክ እና ፍራንስዋ ኦማም ቢይክ (ካሜሮን)
ሁለቱ ወንድማማቾች በሶስት የአፍሪካ ውድድሮች ላይ በጋራ ተሰልፈዋል። ተጨዋቾቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በአህጉራዊ መድረክ በጋራ የመሰለፍ እድል ያገኙት እ.አ.አ በ1988 በሞሮኮ አስተናጋጅነት በተካሄደው 16ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው።
እ.አ.አ በ1990 በአልጄሪያ በተካሄደው 17ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እና ሴኔጋል እ.አ.አ በ1992 ባዘጋጀችው 18ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በጋራ ተሰልፈዋል።
ጣልያን እ.አ.አ በ1990 ባዘጋጀችው 14ኛው የዓለም ዋንጫ ከወንድማማቾቹ ታናሹ ፍራንስዋ ኦማም ቢይክ ካሜሮን አርጀንቲናን 1 ለ 0 ባሸነፈችበት ጨዋታ ባስቆጠራት ጎል ሁሌም በሀገሬው ሰዎች ሲወሳ ይኖራል።
5. አንድሬ አየው እና ጆርዳን አየው (ጋና)
ጋናውያኑ ወንድማሞች የአፍሪካ ዋንጫ ሲነሳ ሁሌም የሚታወሱ ተጫዋቾች ናቸው። በስድስት የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ አብረው ተሰልፈዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ አብረው የሰለፉት ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጋቦን እ.አ.አ በ2012 ባዘጋጁት 28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነው።
የአየው ወንድማማቾች እ.አ.አ በ2015 ኢኳቶሪያል ጊኒ ባዘጋጀችው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማንሳት ተቃርበው የነበሩ ቢሆንም በፍጻሜው በኮትዲቭዋር በመለያ ምት ተሸንፈው ህልማቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
የታዋቂው አፍሪካዊ ተጫዋች አብዲ ፔሌ ልጆች የሆኑት አንድሬ እና ጆርዳን አየው እ.አ.አ በ2023 በኮትዲቭዋር አስተናጋጅነት በተካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመጨረሻ ጊዜ በጋራ ተሰልፈዋል።
ጋና እ.አ.አ በ2008 ባዘጋጀችው 26ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጋናዊው አጥቂ አሳሞሃ ጊያን እና ታናሽ ወንድሙ ባፎር አንድ ላይ ተጫውተዋል።
በተጨማሪም በዛው ውድድር ላይ ጋናውያኑ ወንድማማቾች ሪቻርድ ኪንግስተን እና ላሪያ ጊንግስተን አብረው የመጫወት እድል አግኝተዋል።
6. ኮሎ ቱሬ እና ያያ ቱሬ (ኮትዲቭዋር)
በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከሚነሱ ተጫዋቾች መካከል ኮሎ ቱሬ እና ያያ ቱሬ ይጠቀሳሉ።
ወንድማማቾቹ ለመጀመሪያ ጊዜ አብረው የተሰለፉት እ.አ.አ በ2006 በግብጽ አስተናጋጅነት በተካሄደው 25ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነው። በወቅቱ ኮትዲቭዋር ለፍጻሜ ደርሳ በግብጽ ተሸንፋለች።
ኢኳቶሪያል ጊኒ እ.አ.አ በ2015 ባዘጋጀችው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኮትዲቭዋር ጋናን በማሸነፍ ዋንጫውን ለሁለተኛ ጊዜ ስታነሳ በጋራ የድሉ ተቋዳሽ ሆነዋል።
የቱሬ ወንድማማቾች ለስድስት ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫው አብረው ተጫውተዋል።
7. የሞሪታኒያ እና ዛምቢያ ወንድማማች ተጫዋቾች
እ.አ.አ በ2023 ኮትዲቭዋር ባስተናገደችው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሞሪታኒያ ብሄራዊ ቡድን ስብስብ ከሁለት ቤተሰብ በተመሳሳይ ሁለት ወንድማማቾች መሳተፋቸው የተለየ ትኩረት ስቧል።
ኑህ መሐመድ አብድ እና ታናሹ ሲዲ መሐመድ አህመድ አብድ በተከላካይ እና አማካይ መስመር ላይ ተሰልፈው ተጫውተዋል።
ላሚን ባ እና ኤል ሃጂ ባ ለሞሪታኒያ ብሄራዊ ቡድን በመሰለፍ መጫወት ችለዋል።
ዛምቢያዊያኑ ክርስቶፈር እና ፍሊክስ ካቶንጎ እ.አ.አ በ2012 ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጋቦን በጣምራ ባዘጋጁት 28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛምቢያ ኮትዲቭዋር በማሸነፍ የአፍሪካ ዋንጫን ስታነሳ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።
ደቡብ አፍሪካ እ.አ.አ በ2013 ባዘጋጀችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይም በጋራ ተሰልፈው ተጫውተዋል።
ዛምቢያውያኑ ወንድማማቾች ኬኔት እና ሞርዶን ማሊቶሊ እ.አ.አ በ1994 በቱኒዚያ በተካሄደው 19ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እና ደቡብ አፍሪካ እ.አ.አ በ1996 ባዘጋጀችው 20ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አንድ ላይ ተሰልፈዋል።
አለን ትራኦሬ እና ኢብራሂማ ትራኦሬ (ቡርኪናፋሶ) በ30ኛው እና 31ኛው የአፍሪካ ፣ ሳምቡ ያታባሬ እና ሙስጠፋ ያታባሬ (ማሊ) በተመሳሳይ በ30ኛው እና 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ፣ ፒተር ንዶልቩ እና አዳም ንዶልቩ (ዚምባቡዌ) በ24ኛው የአፍሪካ ዋንጫ፣ ሳሉ፣ ባቺሩ እና ታጁ (ቶጎ) በ22ኛው የአፍሪካ ዋንጫ፣ ቾሞጎ ኦማር እና ሴዲያት ኦማር (ቤኒን) በ24ኛው የአፍሪካ ዋንጫ፣ መሐመድ እና ሙሳ ካሎን (ሴራሊዮን) በ20ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እና ሳሚር ሳሊሚና አዴል ሳሊሚ (ቱኒዚያ) በ19ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አብረው የተሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው።
በአፍሪካ ዋንጫ ከተሰለፉ ወንድማማቾች መካከል ስድስቱ የአፍሪካ ዋንጫን ማንሳታቸውን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።