የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2018 (ኢዜአ):- ዘጠነኛው የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም የካቲት 9 እና 10 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሴኤ) ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሁነቱን ያዘጋጃል።
ፎረሙ በአዲስ አበባ በየካቲት ወር ከሚካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን የሚደረግ ነው።
“የአፍሪካን መጻኢ ጊዜ በፋይናንስ መደገፍ፤ ስራ እና ኢኖቬሽን ለዘላቂ ትራንስፎርሜሽን” የፎረሙ መሪ ሀሳብ ነው።
የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም በአፍሪካ የልማት እና የኢኮኖሚ እድገት ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄድ ከፍተኛ አህጉራዊ የምክክር መድረክ መሆኑን ኢዜአ ከኢሲኤ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
አህጉራዊው መድረክ የአፍሪካ መሪዎች፣ ባለሀብቶች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋንያንና የልማት አጋሮችን በአንድ መድረክ የሚያገናኝ ነው።
ፎረሙ አጋርነትና የኢንቨስትመንት መጠንን ማሳደግ በተለይም የመንግስት እና የግል የተቀናጀ የፋይናንስ አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ አማራጮችን ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ይደረጋል።
የስራ ዕድል፣ ምቹ የኢኖቬሽን ስነ ምህዳር እና የአፍሪካን የፈጠራ አቅም አሟጦ መጠቀም በፎረሙ ላይ ምክክር ከሚካሄድባቸው አጀንዳዎች ይጠቀሳሉ።
በተለይም የዲጂታል ኢንዱስትሪዎች፣ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም እየሰፋ ያለውን የአፍሪካ የፈጠራ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶባቸዋል።
በፎረሙ የተለያዩ ኢኒሼቲቮች እና ማዕቀፎች ይተዋወቃሉ።
የወጣቶችን የኢኖቬሽን ስራ ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር የሚያስተሳስር የአፍሪካ የወጣቶች አይበገሬነትና ትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ ይፋ ይሆናል።
በኢሲኤ የበለጸገውና የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ የፋይናንስ ቃል ኪዳኖችን ትግበራ የሚከታታልና የሚቆጣጠር ስርዓትም በፎረሙ ይፋ ሆኖ ወደ ትግበራ ይገባል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ሁነት ላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የምክክር መድረኮችና የባለሙያዎች ውይይቶች ይደረጋሉ።
አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና የፈጣራ ባለሙያዎችን ከባለሀብቶች እና ፋይናንስ አቅራቢዎች ጋር የሚያገናኝ አውደ ርዕይም ይካሄዳል።
ሁነቶቹ ቃል ኪዳኖችን ወደ ተጨበጡ የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች ለመቀየር አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ተመላክቷል።
የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም በዘላቂ ልማት ግቦች እና በአጀንዳ 2063 የተቀመጡ ግቦች እንዲሳኩ ስትራቴጂካዊ ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝ መረጃው አመላክቷል።