ቀጥታ፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ለመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ውጤታማነት ቁልፍ ሚና ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ለመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ውጤታማነት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የፌዴራል መንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለሥልጣን ገለጸ።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመንግስትን የግዥ አሰራር ግልጽነት ለማስፈን የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት (e-GP) ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም በ2018 በጀት ዓመት ሁሉም የፌዴራልና የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚፈጽሙት ግዥ በኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት እንዲፈጸም እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓቱም የሀገር ውስጥና የውጭ ተጫራቾች እኩልና ግልጽ የመጫረቻ ዕድል የሚያገኙበትን ፍትሕዊ አሰራር እያሰፈነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓቱ አማካኝነት ከዕቅድ እስከ ግዥ የሚከናወኑ ሥራዎችን በግልጽ የተጠያቂነት የአሰራር ሥርዓት እንዲመራ በማስቻል ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

የመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትን ውጤታማነት ለማስጠበቅም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን የማስተሳሰር ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

አቅራቢዎችም በግዥ ምዝገባ ወቅት የንግድ ፈቃድ፣ የግብር መለያ ቁጥርና የተጨማሪ ዕሴት ታክስ ምዝገባ ማረጋገጫቸውን በቀጥታ በዲጂታል ሥርዓት የሚያቀርቡበት አሰራር መሆኑንም አንስተዋል።

በተሳሳተ ማንነት የመንግስት ግዥ እንዳይፈጸም ለማስቻልም ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ደረጃውን የጠበቀ ወጥ አሰራር ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም የፌዴራል መንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለሥልጣን ዘመናዊ የግዥ የአሰራር ሥርዓትን በመዘርጋት ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ውጤታማነት የድርሻውን እንደተወጣ አብራርተዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም የመንግስትን የግዥ ሥርዓት ውጤታማነት ለማሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በቀጣይም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መነሻነት ከፌዴራልና ከሁሉም ክልሎች ጋር በመተባበር የግዥ ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክ ሥርዓት ለማስፈጸም ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም