ቀጥታ፡

በክልሉ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የተገኘውን አበረታች ውጤት ዘላቂ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል

አርጎባ፤ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ በክልሉ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የተገኘውን አበረታች ውጤት ዘላቂ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የክልሉ የ2018 ዓ.ም የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በደቡብ ወሎ ዞን አርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ዛሬ ተጀምሯል።


 

በማስጀመሪያው መርሃ ግብር የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ ባለፉት ዓመታት በክልሉ የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን አውስተዋል።

ልማቱ የተፈጥሮ ሚዛንን በማስጠበቅ፣ ምርታማነትን በማሳደግ ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት ማስቻሉን ጠቅሰው፤ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በንብ ማነብና በሌሎችም የተገኘውን አበረታች ውጤት ዘላቂ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

በውሃ ማሰባሰብ ሥራውም ድርቅን በመቋቋም ለመስኖ ልማት አወንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።

የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ዛሬ በይፋ መጀመሩን ገልጸው፤ በቀጣይ እስከ አራት ወራት በንቅናቄ ይሰራል ብለዋል።

ሰላምና ልማት የማይነጣጠሉ በመሆናቸው ሕብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ ልማቱን ሊያስቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ደረጀ ማንደፍሮ፤ የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ከ9 ሺህ በሚበልጡ ተፋሰሶች ላይ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

ሕብረተሰቡን በማሳተፍ 456 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ይከናወናል ብለዋል።

ልማቱ ቀጣይነት ሲኖረው ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የደን ሽፋኑን ለመጨመርና ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።


 

ሕብረተሰቡን አስተባብሮ ልማቱን ከማከናወን ባለፈ በለሙ አካባቢዎች አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ወደ ሥራ መገባቱን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሊ መኮንን ናቸው።

የልማት ሥራው የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የሰብል ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፣ የእንስሳት መኖ ለማልማትና የአፈር እርጥበትን ለማቆየት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ እና በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም