ቀጥታ፡

የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ እንዲዘጋጅ እየተደረገ ነው

አዳማ፤ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፡-የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና ስርዓተ ትምህርቱን መሰረት ያደረጉና የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ እንዲዘጋጅ እየተደረገ መሆኑን ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ገለጸ።

የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ስታንደርድ ማስጠበቅ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ የክልሎችና የከተማ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ ተወካዮች በተገኙበት በአዳማ እየተካሄደ ነው።


 

የመድረኩ መክፈቻ ላይ  የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር)፣ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከሚያግዙ ተግባራት መካከል አንዱ ደረጃውን የጠበቀ ፈተና መስጠት ነው ብለዋል።

አገልግሎቱ በየደረጃው የሚሰጡ ፈተናዎች ስርዓተ ትምህርቱን መሰረት ያደረጉና የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ የ8ኛ ክፍል ፈተና የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ እንዲዘጋጅ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በተለይም ፈተናው ከመሰጠቱ በፊት የተዘጋጁ የፈተና ጥያቄዎችን መመዘንና መገምገም ከትምህርት ዘርፉ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የሚጠበቅ መሆኑን አንስተዋል።


 

የፈተናዎቹ ጥራትና ሚዛናዊነት አንዱ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ለዚህም አገልግሎቱ ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ብለዋል።

በዝግጅቱ ሂደት ቴክኖሎጂን መጠቀም የፈተናውን ጥራትና ሚዛናዊነት እንዲጠበቅ የሚያደርግ ሲሆን በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ ያለውን ክፍተት መሙላት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የዛሬው መድረክ በ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና አሰጣጥ ዙሪያ የነበሩ የአፈፃፀም ክፍተቶችን በመለየት ወጥነት ያለው ዝግጅት ለማድረግ ያለመ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይልቃል ወንድምነህ ናቸው።


 

በተለይ ክልሎች በራሳቸው የፈተናውን ጥራት ለማስጠበቅ በቴክኖሎጂ፣ በአሰራርና አደረጃጀት ያከናወኑት ተግባር ልምድ የሚወሰድበት ነው ብለዋል።

መድረኩ ፈተናን ለማዘጋጀት፣ ለመመዘንና ለመገምገም የሚያስችል አቅምን ለመገንባት ጭምር የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም