ከኢኮኖሚ ስብራት ወደ ኢኮኖሚያዊ ማንሰራራት - ኢዜአ አማርኛ
ከኢኮኖሚ ስብራት ወደ ኢኮኖሚያዊ ማንሰራራት
አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በተለያዩ ዘርፎች ተጨባጭ እና ዘላቂ የእድገት ውጤቶችን በማስመዝገብ ለጠንካራ እና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ መሰረት መጣሉን የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በተለያዩ ዘርፎች ተጨባጭ እና ዘላቂ የእድገት ውጤቶችን በማስመዝገብ ለጠንካራ እና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ መሰረት ጥሏል፡፡
የመንግሥት ቁርጠኝነት በታየበት በዚህ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ለዓመታት በኢኮኖሚው ላይ ተጋርጠው የነበሩ መዋቅራዊ ችግሮች ደረጃ በደረጃ እንዲቀንሱና ውስጣዊ ዐቅም ያለው፣ ከአለም ጋር የተሳሰረ እና በገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዲገነባ አስቻይ ዐውድ መፍጠር ተችሏል፡፡
የኢኮኖሚ እድገቱ በላቀ ደረጃ እንዲፋጠን በተለይ የዋጋ ግሽበትን በማረጋጋት፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችቶችን በማሳደግ፣ ተኪ ምርቶችን በማበረታታትና፣ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፍሰቶችን በመሳብ ረገድ ማሻሻያው በእስካሁኑ ጉዞ ጉልህ ስኬቶችን አስመዝገቧል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን መንግሥት በተከታታይ የወሰዳቸው ቁርጠኛ የማሻሻያ ውሳኔዎች ለተገኘው ስኬት መሰረቶች ናቸው፡፡ መንግሥት የኢኮኖሚ ስብራቱ እንዲጠገንና መልሶ እንዲያንሰራራ ከወሰዳቸው ቁልፍ እርምጃዎችና ካከናወናቸው አንኳር ስራዎች መካከል የውጭ የምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲመራ እና የኢትዮጵያ ገንዘብ ትክክለኛውን ዋጋ እንዲያገኝ መደረጉ ነው፡፡
በዚህም ቀደም ሲል በህገ-ወጥ መንገድ ይዘዋወር የነበረው የውጭ ምንዛሬ ወደ ባንክ ህጋዊ ሥርዓት እንዲገባ በማድረግ በዶላር ዕጥረት ሊዘጉ ከጫፍ የደረሱ የኢንቨስትመንት ተቋማት ወደ ሥራ እንዲመለሱና ኢኮኖሚው ከገጠመው ከባድ ስብራት መልሶ እንዲያገግም ያስቻለ ውጤታማ ሥራ ማከናወን ተችሏል፡፡
ሌላው መንግሥት ካከናወናቸው ቁልፍ ተግባራት የሚጠቀሰው የውጭ ዕዳ ሽግሽግና ስረዛ እንዲደረግ የተሳካ ድርድር ማድረጉ ነው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የወሰደቻቸው ብድሮች ከፍተኛ ወለድ የሚከፈልባቸው እና በአጭር ጊዜ የሚከፈሉ ኮሜርሻል ሎን በመሆናቸው ሀገርን ከባድ ፈተና ውስጥ ከተው ቆይተዋል፡፡
ይህን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ከአበዳሪ አገራትና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ባደረገው ስኬታማ ድርድር 4.5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የዕዳ ሽግሽግ ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህም ሀገሪቱ ለውጭ ዕዳ መክፈያ ስትጠቀምበት የነበረው ሀብት፣ የሀገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ለማሳደግና በመላ ሀገሪቱ እየተከናወኑ ላሉ የልማት ሥራዎች እንዲውል እድል ፈጥሯል፤ የፋይናንስ ተቋማትንም በእጅጉ አጠናክሯል፡፡
ከሁሉም በላይ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው ያስገኘዉ ውጤት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ግልጽና ሊተነበይ የሚችል የምንዛሬ ሥርዓት መፈጠሩ ነው፡፡ በዚህም የውጭ ባለሀብቶች በሀገራችን ላይ ያላቸው እምነት እንዲጎለብት፣ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው ካፒታል እንዲጨምር እና እንደሀገር ሁለተናዊ የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
በጥቅሉ የተደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሀገርን ከውድቀት በመታደግ፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችትን በማሳደግ እና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ጥንካሬ በማጎልበት ከአለም የንግድ ማኅበረሰብ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ እንዲሸጋገር አድርጓል፡፡
የተገኙ ስኬቶች ዘላቂ እንዲሆኑ የወጪ ንግድን (Export) ማሳደግ፣ ተኪ ምርቶችንና ምርታማነትን መጨመር የመንግሥት ዋና ትኩረት ሆነው ይቀጥላሉ፡፡