ቀጥታ፡

በክልሉ የዋጋ ንረትን በዘላቂነት ለመከላከልና ሸማቹን ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ነው

ባሕርዳር፤ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ጥራትና ብዛት ያላቸው ምርቶችን ወደ ገበያ ማዕከላት በማስገባት የዋጋ ንረትን በዘላቂነት ለመከላከልና ሸማቹን ተጠቃሚ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በባሕርዳር ከተማ  አስተዳደር  አምራችና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኝ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶች የቀረቡበት  የገና ዋዜማ ባዛር ተከፍቷል።


 

በባዛሩ ላይ  114 አቅራቢዎች፣ አምራቾች፣ ዩኒየኖችና ሕብረት ስራ ማህበራት ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው መቅረባቸው ተመልክቷል።

‎‎የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም መሃመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ የገበያ ማዕከላት ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።


 

በግንባታ ላይ የሚገኙ ማዕከላትንም በቅርቡ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በቀጣይ ወደማዕከላቱ ጥራትና ብዛት ያላቸው ምርቶችን በማስገባት የዋጋ ንረትን በዘላቂነት ለመከላከልና ሸማቹን ተጠቃሚ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

‎‎ከገበያ ማዕከላቱ በተጨማሪ የድንኳንና ሌሎች የገበያ አማራጮችን በማቅረብ ሸማቹ  የሚፈልጋቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

በባሕርዳር  የተከፈተውና ‎ከዛሬ ጀምሮ ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት የሚቆየው የገና ዋዜማ ባዛር ላይ ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶች ለሸማቹ ማሕበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደቀረቡም አስታውቀዋል።

‎የክልሉ የግብርና ምርቶች መዳረሻ የገበያ ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተዋቸው ወርቁ  እንዳመለከቱት፤ የባዛሩ ዓላማ  አምራችና ሸማቹን በቀጥታ ማገናኘት ነው።


 

‎‎ባዛሩ በማዕከሉ አስተባባሪነት ከክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ፣ ከባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ፣ ከክልሉ ህብረት ስራ ኮሚሽንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንደተዘጋጀም  ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም