የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የቴክኖሎጂ ክህሎት እና ተወዳዳሪነትን አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የቴክኖሎጂ ክህሎት እና ተወዳዳሪነትን አሳድጓል
ሻሸመኔ፤ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ያገኙት የቴክኖሎጂ እውቀት በዘርፉ ያላቸውን ክህሎትና ተወዳዳሪነት እንዳሳደገው የሻሸመኔ ከተማ የኮደርስ ሰልጣኞች ገለጹ።
የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭ 5 ሚሊዮን ዜጎች የቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን በማዳበር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታቅዶ እየተሰጠ ነው፡፡
በሻሻመኔ ከተማ ስልጠናውን የወሰዱ ሰልጣኞች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ እውቀትና ክህሎት እንዳገኙ ተናግረዋል።
መንግስት በነጻ ያመቻቸውን የስልጠና ዕድል ተጠቅመው በተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ሰልጥነው የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፣ ስልጠናው የቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን በማሳደግ በተሰማሩበት መስክ ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደጉን ገልጸዋል።
ስልጠናው ብዙዎች በተጨማሪ የገቢ ምንጭ ላይ ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን የገለጸችው ወጣት መስከረም ደንደና ናት።
በስልጠናው ያገኘችው እውቀት በየትኛውም አካባቢ ሄዳ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆንና የራሷን ሥራ ለመፍጠርም እንደሚያስችላት ተናግራለች።
በሁለት የቴክኖሎጂ ዘርፎች የሚሰጠውን ስልጠና በማጠናቀቅ የምስክር ወረቀት እንዳገኙና ቀሪዎቹን ስልጠናዎች እየተከታተሉ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ ሳፊ ከድር ናቸው።
የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት በመያዝ ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደጉን ገልጸው፣ ስልጠናው ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል።
በአራት የቴክኖሎጂ ዘርፎች የሚሰጠውን ስልጠና በማጠናቀቅ የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን የተናገሩት አቶ አብዮ ጀማል በበኩላቸው፣ ስልጠናው የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን እንዳሳደገው ተናግረዋል።
ያገኙት እውቀት ራሳቸውን ከዓለም ጋር ለማስተዋወቅ፣ ቴክኖሎጂን በተሻለ ለመጠቀምና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት እያገዛቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
በግል ከፍሎ ለመሰልጠን ቢታሰብ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀውን ስልጠና መንግስት በነጻ በማቅረቡ ያመሰገኑት አቶ አብዮ፣ ዜጎች በተለይ ወጣቶች ከዘመኑ ጋር ለመራመድ ዕድሉን ሊጠቀሙበት ይገባል ብለዋል።
በሻሸመኔ ከተማ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብድሮ ፋይሳ ናቸው።
በስልጠናው የመንግስት ሠራተኞች፣ ወጣቶችና ፍላጎቱ ያላቸው ሁሉ እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቁመው እስካሁን ድረስ ከ8 ሺህ በላይ ዜጎች ስልጠና ወስደው ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
ስልጠናውን የወሰዱ የመንግስት ሠራተኞችም የቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን በማሳደግ በስራቸው ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን አስረድተዋል።