ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አሶሳ፤ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ሆሞሻ ወረዳ ፆሬ አልመተማ ቀበሌ ከ17 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የውሃና ስነ ንጽህና ፕሮጀክት ግንባታ ስራ አስጀምረዋል።


 

ፕሮጀክቱ ከዩኒሴፍ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚገነባ ሲሆን 140 ሚሊዮን ብር እንደተመደበለትም ተገልጿል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሳደግ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።


 

በዚህም ከህብረተሰቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒሴፍ እና ሌሎች አጋር አካላትም የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታን ከማከናወን ባለፈ  የውሃ ተቋማቱ ዘላቂነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ በሶላር ኃይል እንዲሰሩ በማድረግ ለንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀጂራ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱን በስድስት ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አብራርተዋል።


 

ፕሮጀክቱ በሆሞሻ ወረዳ ጾሬ አልመተማ፣ ዱንጋ አሩሜላ እና አቀንዶ አፋፍሪ የሚገኙና ከ17 ሺህ በላይ የሚሆኑ የህብተረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ  እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም