የሆሳዕና ከተማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ለኑሮ ምቹ አድርጓል- ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሆሳዕና ከተማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ለኑሮ ምቹ አድርጓል- ነዋሪዎች
ሆሳዕና፤ ታህሳስ 20/2018 (ኢዜአ) ፡-የሆሳዕና ከተማ የኮሪደር ልማትና የአስፓልት መንገድ ግንባታ ከተማዋን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ ማድረጉን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል አቶ ተመስገን ጌታሁን በከተማዋ እየተሰራ ያለው የመንገድና የኮሪደር ልማት ቀደም ሲል በየመንገዱ በሚጣል ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻን ለማስወገድ አስችሏል።
በከተማዋ ኮሪደርን ጨምሮ የተከናወኑ የመሰረት ልማት ሥራዎች ንፁህ አካባቢን በመፍጠር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪ አቶ ደለለኝ ሻንቆ በበኩላቸው፤ የመንገዱ ግንባታ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን በማሳለጥ የስራ እድል ፈጠራን እንዳሳደገው ጠቅሰዋል፡፡
የአስፓልት መንገዱ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡
በከተማው የተገነቡት ዋና እና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በከተማዋ ፈጣን እድገት እንዲመዘገብ ጠቀሜታቸው የጎላ በመሆኑ ለልማቱ የአቅማቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የገለጹት ደግሞ የቦብቾ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብርሃም ሻፊ ናቸው፡፡
መንገዶቹ የትራንስፖርት መጨናነቅን ከማስቀረት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲፋጠን ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ እንዳሉት፤ በከተማዋ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር 15 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የዋና መንገድና ተለዋጭ የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ እየተከናወነ ነው፡፡
ከዚህ ውስጥ የ5 ኪሎ ሜትሩ የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሥራ ተጠናቋል ብለዋል።
በተጨማሪም በከተማ አስተዳደሩና በህብረተሰቡ ተሳትፎ 12 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ነው የገለጹት።
እነዚህ የአስፓልትና የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተማዋን ለነዋሪው ምቹና ፅዱ ከማድረግ ባለፈ ኢንቨስትመንትና ኮንፍረንስ ቱሪዝም እንዲስፋፉ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም አቶ ሳሙኤል አመልክተዋል።