ቀጥታ፡

የፖሊስ ተቋማት ተልዕኳቸውን በብቃት መወጣት እንዲችሉ አስፈላጊውን ግብዓት የማሟላት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦የፖሊስ ተቋማት ተልዕኳቸውን በብቃት መወጣት እንዲችሉ አስፈላጊውን ግብዓትና መሰረተ-ልማት የማሟላት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡ 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ የተገነቡ 32 አዳዲስ የፖሊስ እና የእሳትና አደጋ ሥጋት መከላከያ ተቋማትን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ይበልጥ ለማጠናከር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተገነቡ  የክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች፣ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ማዕከላት፣ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ የፖሊስ ካምፖች እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ናቸው።  


 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ አስተዳደሩ የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ነው።  

እነዚህ ተግባራት የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ እንደሆኑም ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት ፕሮጀክቶች ፖሊስ ከህዝቡ ጋር በቅርበት በመሆን ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከልና አደጋን ለመቀነስ እና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ እንደሆነ ገልፀዋል። 


 

እንዲሁም የፖሊስን አገልግሎት ተደራሽነት ከማሳደግ ባለፈ የጸጥታ አካላት በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ለማስቻል የተከናወኑ መሆናቸውን ከንቲባዋ ገልጸዋል። 

አዲስ አበባን እንደ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መዲናነቷ ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎቿ ምቹ የማድረግ ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ሰላም ለሁሉም ነገር መሠረት ነው ያሉት ከንቲባዋ በዚህም የጸጥታ መዋቅርን በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል የማዘመን ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ጌቱ አርጋው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የከተማዋን እድገት የሚመጥኑና የነዋሪዎችን ደህንነት ይበልጥ የሚያረጋግጡ ተቋማዊ ለውጦች የግድ አስፈላጊ ሆነዋል።

በዚህም የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን ስማርት ሲቲ ለማድረግ የጀመረውን ታላቅ ግብ መሰረት በማድረግ ፖሊስ ስራውን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ስራ በስፋት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

እነዚህ የሪፎርም ስራዎችና የቴክኖሎጂ ትግበራዎች በከተማዋ ሰላምና ጸጥታ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገባቸውን ተናግረው፤ ይህም ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አያልነሽ ሐብተማርያም፤ በዛሬው ዕለት 32 አዳዲስ የፖሊስ እና የእሳትና አደጋ ሥጋት መከላከያ አገልግሎት የሚሰጡ ህንፃዎች ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ ሕንፃዎች በቴክኖሎጂ የተደራጁ፣ ንጹሕ እና ዓለም አቀፍ የታራሚዎች አያያዝ ድንጋጌን ያሟሉ የማረፊያ ክፍሎች ያሏቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ተቋማቱ ለሠራተኞች ምቹ የሥራ ከባቢን የሚፈጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም