ቀጥታ፡

ፎረሙ በክልሎች መካከል ያለው የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲጠናከር ጉልህ ሚና ይጫወታል

ቦንጋ፤ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የአፈ ጉባኤዎች የጋራ ፎረም  በክልሎች መካከል ያለው የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲጠናከር ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተመላከተ፡፡

የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የአፈ ጉባኤዎች የጋራ ፎረም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አዘጋጅነት መካሄድ ጀምሯል።


 

በፎረሙ ማስጀመሪያ ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ እንደተናገሩት፤ ፎረሙ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በመጎብኘትና ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ በመምከር ምርጥ ተሞክሮዎች የሚወሰድበት ነው።


 

ከዚህ በተጨማሪ በክልሎች መካከል ያለውን የእርስ በርስ  ግንኙነት እንዲጠናከር በማድረግ በኩል ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

የፎረሙ ተሳታፊ አፈ ጉባኤዎች በአሁኑ ወቅትም በክልሉ ካፋ ዞን የተለያዩ የልማትና ታሪካዊ የመስህብ ስፍራዎችን እየጎበኙ ነው።

ጉብኝቱን ተከትሎም  የታዩ ጥንካሬዎችና ጉድለቶችን በማንሳት በፎረሙ በጋራ እንደሚመክሩ አቶ ወንድሙ ተናግረዋል።


 

አፈ ጉባኤዎቹ በካፋ ዞን ጥንታዊ የካፋ ነገስታት መናገሻ ስፍራ የሆነውን "ቦንጌ ሽምበቶን" የጎበኙ ሲሆን በቀጣይም በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የተከናወኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎችንም እንደሚመለከቱ ነው የተገለጸው።

በተጨማሪም የውሽውሽ ሻይ ልማትን እንዲሁም በቤንች ሸኮ ዞን የተከናወኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎችና የተፈጥሮ ፀጋዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።


 

በአፈ ጉባኤዎች የጋራ ፎረሙ ላይ  የተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም