በአማራ ክልል 266 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል 266 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ዘር ተሸፍኗል
ደሴ፤ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ከ266 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በደዋ ጨፋ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴና የፍራፍሬ ልማትን ጎብኝተዋል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ እንደገለጹት፣ በክልሉ የበጋ መስኖ ስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት እየተሰራ ነው።
ባለፉት ዓመታት በስንዴ ልማት ላይ በመጣው ውጤት አርሶ አደሩ ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ በመምጣቱ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ባህል እያደረገው እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም በዘንድሮው በጋ የመስኖ ስንዴ ልማት 350 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም ከ266 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን መቻሉን ጠቁመው እቅዱን ለማሳካት በዘመቻ ጭምር የዘር ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህም በቂ ግብዓት በማቅረብ፣ የመካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ በማዋልና አመራሩና ባለሙያው እስከ ታች ወርዶ ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
አሁን ላይ አርሶ አደሩ ቡቃያውን ከአረምና ከተባይ በመከላከል ምርታማነቱን በማሳደግ የምግብ ዋስትናውን ማረጋገጥና ኢኮኖሚውን ማሳደግ ላይ አተኩሯል ነው ያሉት።
በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የደዋ ጨፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሃመድ ጌታቸው እንደገለጹት፣ በወረዳው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በማስፋት ምርታማነትን የማሳደግ ስራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል።
በዘንድሮው የበጋ ወቅትም ከ5 ሺህ 300 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ከ200 ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።
መንግስት በወቅቱ ያቀረበልንን ግብዓት ተጠቅመን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተሳተፍን እንገኛለን ያሉት ደግሞ በደዋ ጨፋ ወረዳ የሸክላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መሀመድ እንድሪስ ናቸው።
ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን በዘር መሸፈናቸውን ጠቁመው ለሰብሉ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ከ20 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።