ቀጥታ፡

አርሶ አደሮች በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በሚያገኙት ገቢ ህይወታቸው እየተሻሻለ መጥቷል 

ጭሮ ፤ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በሚያገኙት ገቢ ህይወታቸው እየተሻሻለ መምጣቱን የምዕራብ ሐረርጌ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከተጀመረ ወዲህ አርሶ አደሮች በልማቱ በንቃት በመሳተፍ  ለራሳቸው እና ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው።

የበጋ መስኖ ልማት ኢንሼቲቭ ቀደም ሲል ስንዴ አብቃይ ያልነበሩ አካባቢዎችን ወደ ልማቱ ከማስገባቱ በተጨማሪ የአርሶ አደሩን የስራ ባህል በመቀየርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።


 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የምዕራብ ሀረርጌ ዞን የቦኬ ወረዳ አርሶ አደሮች፤ የመስኖ ስንዴ ልማቱ በሀገር ደረጃ ከተጀመረ ወዲህ ወደ ልማቱ በመግባት በሚያገኙት ገቢ ህይወታቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል። 

በዞኑ በልማቱ ከተሰማሩ አርሶ አደሮች መካከል ያህያ አደም፣  ዘንድሮ ሁለት ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እያለሙ ይገኛሉ።


 

የበጋ መስኖ ስንዴ ከመጀመሩ በፊት መሬቱ በጋ ላይ ከከብቶች መዋያነት ባለፈ ለልማት ውሎ አያውቅም ነበር ያሉት አርሶ አደሩ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን መሬቱን ወደ ልማት በማስገባት እስከ 50 ኩንታል ምርት እያገኙበት ነው።

ባለፈው ዓመት ያመረቱትን ምርት ከራሳቸው አልፎ ለገበያ አቅርበው ከ300 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል።

ባገኙት ገቢም ፍየሎችንና በሬ በመግዛት ማድለብ መጀመራቸውን ጠቅሰው የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን እየተጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላኛው የቀበሌው አርሶ አደር አህመድ መሐመድ በበኩላቸው፤ ከሌሎች ስድስት አርሶ አደሮች ጋር በመሆን  በበጋ መስኖ ልማት እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ባለፈው ዓመት ያለሙትን የስንዴ ምርትም ከራሳቸው አልፎ ለገበያ ማቅረብ የቻሉ ሲሆን በዚህም ከ200 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

የቦኬ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መሐመድዘይን ጀማል እንዳሉት፤ በዚህ ዓመት በወረዳው 10 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ ነው።


 

አርሶ አደሮቹ  ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና ግብአት በመጠቀም በልማቱ ውጤታማ እንዲሆኑ በባለሙያ የቅርብ ድጋፍና እገዛ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

በዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አስተባባሪ አቶ ሀቢብ አብዱልከሪም እንደገለጹት፤ በዞኑ ከ50 ሺህ በላይ አርሶአደሮችን በማሳተፍ ከ81 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የማልማት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

እስካሁንም ከ26 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት በዘር  መሸፈኑን በማንሳት በዞኑ ባለፉት ዓመታት እየተከናወነ ያለው የበጋ መስኖ ልማት ስራ ህዝቡን ከተረጂነት ለማላቀቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ 15 ወረዳዎች እየተከናወነ ባለው ልማትም ከሶስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አመልክተዋል።

የምዕራብ ሀረርጌ ዞን የበጋ መስኖ ልማት ስራ ቀደም ብሎ ከሚጀምርባቸው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች አንዱ ሲሆን የዘንድሮ በጋ መስኖ ልማት ስራም ከመስከረም መጨረሻ ጀምሮ ሲካሄድ መቆየቱ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም