ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ስራ ለማስጀመር የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል 

ባህር ዳር ፤ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በጥናት ለተለዩ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ዕውቅና ለመስጠት እና ስራ ለማስጀመር የሚያስችል ዝግጅት ማጠናቀቁን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት  አስታወቀ።

የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ዓለምአንተ አግደው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ፍርድ ቤቱ የባህል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋምና ዕውቅና ለመስጠት የተለያዩ የማስተግበሪያ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

ይህንን መሰረት በማድረግም ዝርዝር የሆነ ዕውቅና መስጫና የማስተግበሪያ መመሪያ እንዲሁም የትግበራ ፍኖተ ካርታ፣ የስልጠናና የተግባቦት ስትራቴጂ ቀረፃ ስራ ማጠናቀቁን ተናግረዋል። 

ለዚህም የፊታችን ታህሳስ 21 እና 22 ቀን 2018 ዓ.ም በክልል ደረጃ ለባህላዊ ፍርድ ቤቶች የዕውቅናና የስራ ማስጀመሪያ መድረክ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

በመድረኩም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ከየወረዳው የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች፣ አዋጁን ለማስፈፀም ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

በዕለቱም የአካባቢውን ባህል፣ ወግና እሴት መሰረት ባደረገ አግባብ በጥናት ለተለዩ 15 አይነት አለመግባባቶችና የሙግት መፍቻ እውቅና እንደሚሰጥ አመልክተዋል።

በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በሚገኙ ከአራት ሺህ በሚበልጡ ቀበሌዎች ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ተደራሽ በማድረግ ስራቸውን በይፋ እንደሚጀምሩም አስታውቀዋል።

ባህላዊ ፍርድ ቤቶች መደበኛ ፍርድ ቤቶችን የሚተኩ ሳይሆን አማራጭ የሙግት መፍቻ ሆነው የህብረተሰቡን ባህላዊ እሴት በጠበቀና ባከበረ መልኩ የሚቀርቡ ጉዳዮችን በማከራከር እንዲፈቱ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።

ይህም የህብረተሰቡ ባህል እንዲዳብርና እሴቱ ተጠብቆ እንዲቀጥል ከማድረግ ባለፈ ተገልጋዮች ባህላዊ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ውሳኔ እንዲቀበሉም ህጉ እንደሚያስገድድ አስረድተዋል።

ዕውቅና የሚሰጣቸው ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የባህል እሴትንና ህጎችን ጠብቀው ሰብዓዊ መብትና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ባከበረ መልኩ ነፃ፣ ገለልተኛና ተአማኒነት ያለው ፍትህ እንደሚሰጡም ገልጸዋል።

ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የመደበኛውን ፍርድ ቤት ጫና የሚያቃልሉ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም