ፋሲል ከነማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ፋሲል ከነማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል።
ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ፋሲል ከነማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ፋሲል ከነማ ባደረጋቸው በሊጉ 11 ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ ስድስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ላይ ዘጠኝ ግቦቹን ሲያስቆጥር ሶስት ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ21 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
በሊጉ እስከ አሁን ሽንፈት ያላስተናገደው ብቸኛ ክለብ ፋሲል ከነማ ነው።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድር ዓመቱ 11 ጨዋታዎችን አድርጎ አምስቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። ስምንት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ አራት ግቦች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በ20 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። ፋሲል ከነማ ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ከሲዳማ ቡና በጊዜያዊነት ይረከባል።
በሌላኛው መርሃ ግብር መቀሌ 70 እንደርታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ምሽት 12 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች መካከል ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አምስት ጊዜ ሲሸነፍ በተመሳሳይ አምስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 12 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ስድስት ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በሰባት ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ 11 ጨዋታዎችን አከናውኖ አምስቱን ሲያሸንፉ አራት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በ11ዱ ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ ሰባት ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ17 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ጨዋታው መቀሌ 70 እንደርታ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከባህር ዳር ከተማ ይጫወታሉ።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በስምንት ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ባህር ዳር ከተማ በ14 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል።
ወላይታ ድቻ ከአርባ ምንጭ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ወላይታ ድቻ በ10 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። አርባምንጭ ከተማ በአምስት ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል።
አርባምንጭ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ምንም ጨዋታ ያላሸነፈ ብቸኛው ቡድን ነው።
ሲዳማ ቡና ሊጉን በ22 ነጥብ እየመራ ነው።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት እስከ ታህሳስ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።