ቀጥታ፡

በአፍሪካ ዋንጫ ወደ ጥሎ ማለፍ የሚገቡ አገራት የሚለዩባቸው ወሳኝ ጨዋታዎች ይደረጋሉ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ።

በምድብ አንድ አዘጋጇ ሀገር ሞሮኮ ከዛምቢያ ምሽት አራት ሰዓት ላይ በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ጨዋታዋን ታደርጋለች።

ሞሮኮ በምድቡ እስከ አሁን ሁለት ጨዋታዎች አድርጋ በአራት ነጥብ ምድቡን እየመራች ነው። ተጋጣሚዊ ዛምቢያ በሁለት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች።

አዘጋጇ ሀገር ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ወደ ጥሎ ማለፍ በቀጥታ ያስገባታል። ተሸንፋም ምርጥ ሶስተኛ ሆና የማለፍ እድል አላት።

ተጋጣሚዋ ዛምቢያ ወደ 16 ውስጥ የመግባት እድሏን ለማስፋት ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

በዚሁ ምድብ በተመሳሳይ ምሽት አራት ሰዓት ላይ  ኮሞሮስ ከማሊ በመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ኮሞሮስ በአንድ ነጥብ አራተኛ፣ ማሊ በሁለት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።

ኮሞሮስ ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ያላት ብቸኛ እድል ማሸነፍ ብቻ ነው። በአንጻሩ ማሊ ወደ 16 ውስጥ የመግባት እድሏ ሰፊ ነው።

በተያያዘም የምድብ ሁለት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ። 

አንጎላ ከግብጽ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ በአጋዲር ስታዲየም ይጫወታሉ።

ከሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ያገኘችው አንጎላ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ ይዛለች።

አስቀድማ ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቷን ያረጋገጠችው ግብጽ በስድስት ነጥብ ምድቡን እየመራች ነው። 

አንጎላ ወደ ጥሎ ማለፉ ለመግባት የሚያስችላትን እድል ለማግኘት ግብጽ ማሸነፍ ይኖርባታል። ጨዋታው ለግብጽ ምድቡን በበላይነት ከማጠናቀቅ የዘለለ ትርጉም የለውም። 

በዚሁ ምድብ በተመሳሳይ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ዚምባቡዌ ከደቡብ አፍሪካ በማራካሽ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ዚምባቡዌ በአንድ ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች። ወደ ጥሎ ማለፍ ለማግባት ያላት ብቸኛ አማራጭ ማሸነፍ ብቻ ነው።

በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ደቡብ አፍሪካ ማሸነፍ ቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ ያስገባታል። አቻ መውጣትን ወደ ቀጣዩ ዙር ሊያሳልፋት ይችላል። 

በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ዘጠነኛ ቀኑን ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም