ቀጥታ፡

አልጄሪያ ጥሎ ማለፍ የገባች ሶስተኛ ሀገር ሆናለች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2018(ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ አምስት ጨዋታ አልጄሪያ ቡርኪናፋሶን 1 ለ 0 አሸንፏል።

ማምሻውን በፕሪንስ ሙላይ ኤል ሀሰን ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሪያድ ማህሬዝ በ23 ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።

ማህሬዝ በአፍሪካ ዋንጫው ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ ሶስት ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት መሪነቱን ይዟል።

በጨዋታው ላይ አልጄሪያ የተሻለ ብልጫ ወስዳለች።

ፈረንሳዊው የቀድሞ ኮከብ ዚነዲን ዚዳን ለአልጄሪያ በግብ ጠባቂነት የሚጫወተውን ልጁን ሉካ ዚዳንን ለተከታታይ ጨዋታ በስታዲየም ተገኝቶ ተከታትሏል።

ሉካ በአፍሪካ ዋንጫው በተሰለፈባቸው ሁለት ጨዋታዎች ግብ አልተቆጠረበትም።

በምድብ አምስት ሁለተኛ ድሏን ያስመዘገበችው አልጄሪያ በስድስት ነጥብ ከግብጽ እና ናይጄሪያ በመቀጠል ጥሎ ማለፍ የገባች ሶስተኛ ሀገር ሆናለች።

ቡርኪናፋሶ በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

በዚሁ ምድብ ዛሬ በተደረገ ጨዋታ ሱዳን ኢኳቶሪያል ጊኒን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

የምድብ አምስት የመጨረሻ መርሃ ግብር ረቡዕ ታህሳስ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል። ኢኳቶሪያል ጊኒ ከአልጄሪያ እና ሱዳን ቡርኪናፋሶ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም